ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና ስሑል ሽረ ነጥብ ተጋርተዋል

ከፕሪምየር ሊጉ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል የወራጅነት ስጋት ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻ እና ስሑል ሽረ ሶዶ ላይ 1-1 በሆነ ወጤት ተለያይተዋል።

በሁለተኛው ዙር የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረግ እና በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማዘዋወር ወደ ውድድር የተመለሱት ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት እንደመደረጉ ተጠባቂ ሆኖ ነበር። የዕለቱ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ የወላይታ ድቻ የደጋፊዎች ማህበር ደጋፊዎችን በማስተባበር ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ አየርመንገድ አውሮፕላን ላይ በደረሰው አደጋ ህይወታቸው ለለፉ ዜጎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ሲያደርጉ ፤ በተጨማሪም በጌድዮ አከባቢ ለተፈናቀሉ ዜጎች ገቢ የማሰባሰቢያ ሥነ ስርዓትም አከናውነዋል።

በዚህ መልኩ 9:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ ወላይታ ድቻዎች በረጃጅም እና ወደ መስመር በሚያመዝኑ ኳሶች ግብ ለማግኘት ጫና የፈጠሩ ሲሆን ገና በ3ኛው ደቂቃ ላይ በስሑል ሽረ ተከላካዮች ንክኪ ጎል ስር የተገኘውን ጥሩ አጋጣሚ ፀጋዬ አበራ በጎሉ አናት ልኮታል። ድቻዎች ይህንን ጫና በመቀጠል ሽሬ የግብ ክልል በተደጋጋሚ የደረሱ ሲሆን በዚህም ሂደት በግራ የግቡ ጠርዝ ላይ በ10ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘችውን ቅጣት ምት ራሱ ባዬ መትቶ ግሩም የሆነ ግብ በማስቆጠር ድቻን መሪ አድርጓል። ባዬ ከቅጣት ምት በቀጥታ ሲያስቆጥር በዚህ አመት ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ከዚህች ጎል መቆጠር በኋላ ሽረዎች ከገቡበት ጫና ለመውጣት ከድቻ በተሻለ መልኩ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ነገር ግን የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ የነበረ ሲሆን በአንፃሩ ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት 16ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በግራ መስመር በጥሩ ሁኔታ አልፎ ኳስ ቢያሻግርም ሰንደይ ሮቲሚ በፍጥነት ይዞታል። በድጋሚ ድቻዎች በ29ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከቀኝ መስመር የተገኘውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ በጥሩ ሁኔታ ወደግብ ሲያሻግር ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ፀጋዬ አበራ ኳሷን ቢሞክርም ከግቡ አናት ላይ ወጥታበታለች። ሽሬዎች ከ35 ደቂቃ በኋላ አብዛኛውን ደቂቃ ኳሱን በመቆጣጠር እና ጫና በመፍጠር በድቻ የግብ ክልል ቢያሳልፉም በ40ኛው ደቂቃ ዮናስ ግርማይ ሞክሮ በግቡ ታካ ከወጣችው ጥሩ ቅጣት ምት ውጪ ግልፅ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ የመጀመርያው አጋማሽ በድቻ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

የሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ከመጀመርያው ይልቅ ጥሩ ፉክክር የታየበት ሲሆን በተለይም ሽረዎች ክፍሎም ገብረህይወትን አስግበተው አርዓዶም ገብረህይወትን በማስወጣት እና የቅርፅ ለውጥ በማድረግ ሙሉ ለሙሉ ጨዋታውን መቆጣጠር ችለዋል። በአንፃሩ ድቻዎች እጅግ ተዳክመው እና ቅርፃቸውን አጥተው ተቸግረው አምሽተዋል። እንግዶቹ በጨዋታው ኮከብ ሆኖ ባመሸው ደሳለኝ ደባሽ እና አሳሪ አልመሐዲ መሀል ሜዳውን የተቆጣጠሩ ሲሆን በሁለቱም መስመሮች አብዱሰላም አማን እና ክፍሎም ገብረህይወት አንዲሁም አጥቂው ቢስማርክ አፒያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለባለሜዳዎቹ ፈታኝ ነበር። በዚህም መሰረት በ49ኛው ደቂቃ ላይ ክፍሎም በግሩም ሁኔታ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ አብዱለሰላም አማን አግኝቶ ቢሞክረም ወደ ወጪ የወጣበት የመጀመርያ የግብ ሙከራ ሲሆን ሽረዎች በተደጋጋሚ ጫና በመፍጠር የማዕዘን ምቶችን ሲያገኙ ቆይተው በ51ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተላከውን ኳስ ተከላካዮች ከግብ ቢያርቁም ከሳጥን ውጪ ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ደሳለኝ ደባሽ ኳስ መሬት ላይ ሳታርፍ በመምታት እጅግ ማራኪ በሆነ መልኩ በድቻ መረብ ላይ አሳርፏል።

ከግቡ መቆጠር በኃላም ሽሬዎች ጫና በፍጠር በ60ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ አሳሪ በግንባሩ ገጭቶ ሙከራው የግቡን አግዳሚ በመንካት በሚያሰቆጭ መልኩ ወደ ውጪ ወጥታበታለች። ጨዋታው በሽሬ የተደራጀ አጨዋወት ለረጅም ደቂቃ የቆየ ሲሆን ጫና ውስጥ የነበሩት ድቻዎች ከ82 ደቂቃ በኃላ በረጃጅም ኳሶች ወደ ሽሬ የግብ ክልል ለመግባት ሲሞክሩ ተስተውለዋል። በተለይም ተቀይሮ የገባው አንዱዓለም ንጉሴ በ83ኛው ደቂቃ ላይ ከእሸቱ መና የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ የወጣችበት ሲሆን በ90ኛው ደቂቃ ደግሞ በዕለቱ አጨቃጫቂ የሆነ ክስተት ተፈጥሯል። ይህም ባዬ ገዛኃኝ ግብ ክልል ስር ያገኛትኝ ኳስ አክርሮ ሲመታ ሰንዴይ ሮቲሚ ለማዳን ጥረት ቢያደርግም ከእጁ ስር በማለፍ ወደ ግቡ መስመር የተጠጋችውን ኳስ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ የነበረ የሚመስለው ፀጋዬ አበራ ወደ ግብነት ቢቀይራትም የዕለቱ ረዳት ዳኛ ጎሉን ሳያፀድቀው ቀርቷል። በመሆኑም የድቻ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ጨዋታውን በመሩት ዳኞች ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተስተውሏል። ጨዋታውም ተጨማሪ 4 ደቂቃዎችን አስተናግዶ ለውጥ ሳይታይበት 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *