ሪፖርት | ደቡብ ፖሊስ በአዲስ አበባ ስታድየም ዛሬም ድል ቀንቶታል

የየተሻ ግዛው እና ኄኖክ አየለ ሁለት ግቦች እርጋታን የተላበሰው ደቡብ ፖሊስን በጨዋታ ብልጫ የታጀበ የ2-0 ድል በመከላከያ ላይ እንዲያስመዘግብ አድርገውታል።

የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራው ደቡብ ፖሊስ ከፍተኛ ብልጫ የታየበት ነበር። ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ማግኘት የቻሉት እንግዶቹ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ኳስ ከመያዝ ባለፈ ወደ ተጋጣሚያቸው አጋማሽ አመዝነው መንቀሳቀስም አልከበዳቸውም ነበር። ሆኖም ቅብብሎቻቸው ወደ ሦስቱ አጥቂዎቻቸው ሲደርሱ ይቋረጡባቸው ነበር። ባልተጠበቀ ሁኔታ ወርደው የታዩት መከላከያዎች 4-3 የሆነ የቁጥር ብልጫ የነበረው አማካይ ክፍላቸው ተሰብሮ ከአጥቂዎቻቸው ጋር በፍፁም ማመገናኘት ተስኗቸው ታይተዋል። 16 ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ካሻማው እና ከተጨረፈ ኳስ አዲሱ በመቀስ ምት ሞክሮ ወደ ውጪ በወጣበት አጋጣሚ ብቻ ነበር ወደ ግብ መድረስ የቻሉት።

በዮናስ በርታ ፣ በዘላለም ኢሳያስ እና ብሩክ አየለ የአማካይ ክፍል ጥምረት በተረጋጋ ፍሰት መጫወታቸውን የቀጠሉት ፖሊሶች ጫን ብለው ሳጥን ውስጥ መድረስ የጀመሩት ከ16ኛው ደቂቃ በኋላ ነበት። ብሩክ ከግራ መስመር አጥቂው የተሻ ግዛው የደረሰውን ኳስ ሳጥን ውስጥ በግልፅ አግኝቶ በቮሊ ሞክሮ የሳተበት ኳስም ከባዱ ሙከራ ነበር። ሆኖም በደቂቃ ልዩነት በረከት ይስሀቅ ከቀኝ መስመር ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ የተሻ ግዛው የቀድሞ ክለቡ ላይ ማስቆጠር ችሏል። ከዚህ ግብ በኋላ መከላከያዎች ከመጀመሪያው በተሻለ ረዘም ባሉ ኳሶች ወደ ፊት ጠጋ ማለት ቢችሉም እርጋታ ያልተለየው እና በፍላጎት ደረጃ ከተጋጣሚው እጅግ ተሽሎ የታየው የደቡብ ፖሊስን የመከላከል ቅርፅ ማስከፈት አልቻሉም።

አማካዮቻቸውን ወደ ኋላ በጥቂቱ ስበው ኳስ በሚያገኙበት ቅፅበት በመስመር አጥቂዎቻቸው የተሻ እና በረከት ፈጣን ጥቃት ይሰነዝሩ የነበሩት ደበብ ፖሊሶች የተጋጣሚያቸው ጫና ሳይሰማቸው ቅብብሎችን ይከውኑ የነበረበት መንገድ አስገራሚም ጭምር ነበር። 27ኛው ደቂቃ ላይም ከቀኝ አቅጣጫ በተነሳ እጅ ውርወራ እና የተለመደው የመከላከያ የኋላ መስመር ስህተት የታከለበትን ኳስ ኄኖክ አየለ ከብሩክ አየለ በመቀበል አስቆጥሮ የቡድኑን ብልጫ በግብ የታጀበ እንዲሆን አድርጓል። ጨዋታው ወደ እረፍት ሊያመራ ጥቂት ሲቀረው የተሻ ተጨማሪ ነፃ አጋጣሚ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቶ ነው እንጂ የእንግዶቹ መሪነት ወደ ሦስት ከፍ ሊል ተቃርቦ ነበር።

የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ አዝናኝነቱ ከመጀመሪያው ቢቀንስም ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም። ጨዋታውን 2-0 መምራት የቻሉት ደቡብ ፖሊሶች ከኄኖክ አየለ በቀር የመስመር አጥቂዎቻቸውን ወደ ኋላ በመሳብ ይበልጥ ተጠንቅቀው ሲጫወቱ ታይቷል። በአብዛኞቹ ደቂቃዎችም የጦሩ ጥቃት ወደ ሳጥናቸው እንዳይገባ ማድረግ ችለው ነበር። ያም ቢሆን ለመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ዝግጁ ያልነበሩት ፖሊሶች በቁጥር በልጠው መሀል ሜዳውን መሻገር የቻሉባቸውን ጥሩ ቅፅበቶች ቢያገኙም ወደመጨረሻ የግብ አጋጣሚነት መቀየር አልሆነላቸውም። በተለይም የየተሻ የዘገዩ ውሳኔዎች ውጤቱ ከዚህም በላይ እንዳይሰፋ አድርገዋል። የተሻ 54ኛው ደቂቃ ላይ 3-1 በሆነ የቁጥር ብልጫ ሳጥን ውስጥ ገብቶ በማቀበል እና በመሞከር መሀል ሆኖ ያመከነው ኳስ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነበር።

ተጋጣሚያቸው በራሱ ማዳ ላይ መቅረቱን ተከትሎ ኳሱን የመያዝ ነፃነት ያገኙት መከላከያዎችም ግብ ጠባቂው ሀብቴ ከድርን መፈተሽ የቻሉት በጥቂት ደቂቃዎች ነበር። ተነሳሽነታቸው ተቀዛቅዞ የታዩት ባለሜዳዎቹ ጫናቸው በርትቶ ታየ ሊባል የሚችለው ከ 77ኛው እስከ 81ኛው ደቂቃ ብቻ ነበር። በእነዚህ ጊዜያት ቡድኑ ሳጥን ውስጥ ከቅርብ ርቀት ንፁህ የሚባሉ ዕድሎችን ጭምር ፈጥሮ ነበር። በወቅቱ ግብ ጠባቂው ሀብቴ የፍሬው ሰለሞንን ሁለት አንድ ደግሞ የሳሙኤል ታዬን ሙከራዎች ማዳን ነበረበት። 81ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ወጣቱ አጥቂ ይታጀብ ገብረማርያም ተጫዋቾችን አልፎ ሳጥን ውስጥ ያመቻቸው እና በዳዊት ማሞ የተሞከረውም ኳስም በሀብቴ ጥረት ድኗል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ግን ጦሩ ድንቅ ሆነው ያመሹትት ደቡብ ፖሊሶችን ዳግም ማስከፈት ተስኖት ጨዋታው በመጀመሪያው የ2-0 ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *