ሴቶች አንደኛ ዲቪዝዮን | በ17ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች አአ ከተማ እና ጥረት አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን 17ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ አዲስ አበባ ከተማ እና ጥረት ኮርፖሬት ድል አስመዝግበዋል።

08:00 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የልምምድ ሜዳ የተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ በአዲስ አበባ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሴቶች ስፖርት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ትዕንግርት የሴቶች ስፖርት ለኢትዮ ኤሌክትሪክ የመስመር አጥቂ መሳይ ተመስገን የእውቅና ሽልማት በመስጠት በተጀመረው ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ከቡድኑ ዋና አሰልጣኝ መስረት ማኒ ጋር መለያየቱን እስካሁን በይፋ ክለቡ ባያሳውቅም ያለፉት አራት ጨዋታዎችን በምክትል አሰልጣኞቹ እየተመራ እያሳየ ባለው ከፍተኛ መሻሻል ቀጥሎ ዛሬም በጥሩ ጨዋታ አሸንፎ ወጥቷል።

ኢትዮ ኤሌትሪኮች አጀማመራቸው መልካም ቢሆንም በክፍት ጨዋታ የጎል አጋጣሚ የመፍጠር ድክመት ሲታይባቸው ከቆሙ ኳሶች ጎሎችን ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት በአዲስ አበባዎች ግብጠባቂ ስርጉት ተስፋዬ ይመክንባቸው ነበር። ለዚህም ማሳያ በሁለት አጋጣሚ ዓለምነሽ ገረመው ከቅጣት ምት የሞከረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ያዳነችው ተጠቃሽ ነው።

የቀድሞው የፌስቡክ ገፃችን በኛ ቁጥጥር ስር የማይገኝ በመሆኑ አዲሱ ገፃችንን ሊንኩን በመከተል ላይ ያድርጉ – facebook.com/SoccerEthiopia

ከእነዚህ የግብ ዕድሎች መፈጠር በኋላ መዳከም እና በሚቆራረጡ ኳሶች በቀላሉ ይነጠቁ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ተወስዶባቸዋል። በተለይ በመሐል ክፍሉ ላይ ብልጫ የወሰዱት አዲስ አበባዎች አማካይዋ ህይወት ረጉ በግሏ እና ከቡድኑ የምታደርገው እንቅስቃሴ ብልጫ ለመውሰዳቸው ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። 13ኛው ከቅጣት ምት ህይወት የግቡ አግዳሚ የመለሰባት፤ ብዙም ሳይቆይ ራሷ ህይወት በድጋሚ ከቅጣት ምት ሞክራ ግብጠባቂዋ እስራኤል ከተማ ያዳነችባት በመጀመርያው አጋማሽ ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ከእረፍት መልስ ከኤሌክትሪክ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት አዲስ አበባዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ኤደን ሽፈራው ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኗን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች። ኢትዮ ኤሌትሪኮች አቻ መሆን የሚችሉበትን አጋጣሚ የአዲስ አበባ ተከላካይ እታፈራው አድርሴ ኳሱን ለመቆጣጠር ስታስብ ተንሸራታ መውደቋን ተከትሎ ስትወድቅ ዓይናለም ነፃ ኳስ አግኝታ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። በአዲስ አበባ በኩል ህይወት ረጉ የግብጠባቂዋን አቋቋም አይታ ቺፕ አድርጋ መትታ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣውም የሚያስቆጭ ነበር።

70ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም ሰማን በጥሩ መንገድ ለግብ የቀረበ ኳስ አቀብላት በዕለቱ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የዋለችው ህይወት ረጉ ወደ ጎልነት በመቀየር የአዲስ አበባን መሪነት ወደ ሁለት አስፍታለች። በከፍተኛ የመጫወት ፍላጎት ላይ የሚገኙት አዲስ አበባዎች ውጤቱን አስጠብቀው 2-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሦስት ነጥብ ይዘው ሊወጡም ችለዋል።

አርባምንጭ ላይ በተደረገው የ17ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ጥረት ኮርፖሬት 3-0 ማሸነፍ ችሏል። ምስር ኢብራሂም ሁለት፤ ትዕግስት ወርቁ ቀሪዋን አንድ ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ማጣርያ ከዩጋንዳ ጋር ለሚጠብቃት ጨዋታ በቀናት ውስጥ ዝግጅት የሚጀመር ሲሆን በዚህም ምክንያት ሊጉ ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚቋረጥ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *