የሴቶች ኦሊምፒክ ቡድን ዝግጅቱን ጀመረ

በ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ የማጣርያ ውድድር መጋቢት 25 አዲስ አበባ ስቴዲየም ላይ ዩጋንዳን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ጀምሯል።

አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ ለ30 ተጫዋቾች የመጀመርያ ጥሪ ካደረገች በኋላ ከትናንት ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ የተሰባሰበው ቡድን ዛሬ ቀትር 08:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት ዝግጅቱን ጀምሯል። ጥሪ ከተደረገላቸው 30 ተጫዋቾች መካካል የሉሲዎቹ አምበል የነበረችው ረሂማ ዘርጋው በጉዳት ምክንያት ከብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውጭ ስትሆን የተቀሩት 29 የቡድኑ አባላት በሙሉ በዛሬው ልምምድ ላይ ተሳትፈዋል።

የውድድሩ ቀን በመቃረቡ ምክንያት 23 ተጫዋቾችን በፍጥነት ለመለየት በሦስት ምድብ ተከፍለው ሙሉ ሜዳ እንዲጫወቱ በማድረግ የአሰልጣኝ ቡድኑ አባላት አሁን ያሉበትን ወቅታዊ አቋም የመለየት ስራ ሲሰሩ ተመልክተናል።

ረቡዕ መጋቢት 25 የመጀመርያ ጨዋታቸውን በአዲስ አበባ ስቴዲየም የሚያደርጉት ሉሲዎቹ የመልስ ጨዋታቸውን ከሦስት ቀን በኃላ በካምፓላ የሚያደርጉ ይሆናል። ብሔራዊ ቡድኑ በደርሶ መልስ ጨዋታ ድል የሚቀናው ከሆነ ቀጣይ ተጋጣሚ ካሜሩን እንደምትሆን ካፍ አሳውቋል።

*ሉሲዎቹ በዛሬው ልምምድ ብሔራዊ ቡድን በማይወክል የተዘበራረቀ ማልያ እና የቀድሞ የብሔራዊ ቡድኑ የትጥቅ አቅራቢ በነበረውና በቅርቡ የውል ስምምነቱ የተቋረጠው ኢርያን ጥትቅ በመልበስ ልምዳቸውን ሰርተዋል። ይህ በቀጣይ መስተካከል ያለበት መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *