ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ጅማ አባ ጅፋር

ከነገ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ውስጥ መከላከያ እና አባ ጅፋር የሚገናኙበትን ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።

የአዲስ አበባ ስታድየም ነገ 10፡00 ላይ መከላከያ እና ጅማ አባ ጅፋር የሚገናኙበትን የ17ኛ ሳምንት ጨዋታ ያስተናግዳል። በተስተካካይነት ተይዞ በመጀመሪያ ዙር መገባደጃ ላይ በተደረገው ጨዋታ በነገ ተጋጣሚው ተሸንፎ አመቱን ያጋመሰው መከላከያ ሳምንት በደቡብ ፖሊስ ከሰፊ ብልጫ ጋር ሌላ ሽንፈት አስተናግዷል። ከደደቢት እና ቡና ተከታታይ ድል በኋላም ወደ ውጤት ማጣቱ ተመልሶ ለወራጅ ቀጠናው በመቅረብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከዋንጫ ፉክክሩ በእጅጉ ርቆ 10ኛ ላይ የተቀመጠው የአምናው ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋርም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አሸናፊ መሆን አልቻለም። በመሆኑም በነገው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች የውድድር ዓመቱ አካሄዳቸውን ለማስተካከል እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

በምንይሉ ወንድሙ እና ተመስገን ገብረኪዳን ጉዳት የፊት መስመራቸው የሳሳው መከላከያዎች ፍቃዱ ዓለሙ እና ቴዎድሮስ ታፈሰንም ለኦሊምፒክ ቡድኑ በማስመረጣቸው የማይጠቀሙባቸው ይሆናል። ከመከላከል ችግሩ ባለፈ የተሻለ የሚባለው የመሀል ክፍሉ ለተጋጣሚዎች እጅግ ቀላል እየሆነ የመጣው መከላከያ ነገም በአባ ጅፋር የመሀል ሦስትዮሽ ጥምረት ብልጫ እንዳይወሰድበት ያሰጋዋል። በአንፃሩ ከመሀል በሚነሱ ኳሶች የመስመር አጥቂዎቻቸውን ፍጥነት ተጠቅመው የሚያጠቁት ጅማ አባ ጅፋሮች ምንም የጉዳት እና ቅጣት ዜና የሌለባቸው ሲሆን ዳግም ያስፈረሙት አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ በመጀመሪያ አሰላለፍ አልያም በተጠባባቂነት ጨዋታውን እንደሚጀምርም ይጠበቃል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ጅማ አባ ጅፋር በሊጉ ከመከላከያ ጋር ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት አልገጠመውም። በጨዋታዎቹ ሦስት ግቦች ያስቆጠረው አባ ጅፋር ሁለት ጊዜ አሸንፎ አንዴ ነጥብ ሲጋራ መከላከያዎች አንድ ግብ ብቻ አስቆጥረዋል።

– አዲስ አበባ ላይ ሰባት ጊዜ የክልል ቡድኖችን የገጠመው መከላከያ አንድ ጊዜ ብቻ ድል ሲቀናው ሦስቴ ነጥብ ተጋርቶ ሦስቴ ተሸንፏል።

– ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳ ውጪ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ሁለቴ በድል ሁለቴ ደግሞ በአቻ ውጤት ሲመለስ አራት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል።

ዳኛ

– ጨዋታውን ዮናስ ካሳሁን በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን ሦስት ጨዋታዎችን የዳኘ ሲሆን አስር የማስጠንቀቂያ ካርዶችን መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

ይድነቃቸው ኪዳኔ

ሽመልስ ተገኝ – አዲሱ ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ታፈሰ ሰረካ

አማኑኤል ተሾመ

ዳዊት ማሞ – ፍሬው ሰለሞን

ዳዊት እስጢፋኖስ

ፍፁም ገብረማርያም – ይታጀብ ገብረማርያም

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ዳንኤል አጄዬ

ዐወት ገ/ሚካኤል – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ

ይሁን እንዳሻው – ንጋቱ ገብረስላሴ – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *