ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደቡብ ፖሊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ


ሌላኛው የደቡብ ፖሊስ እና ድሬዳዋ ከተማ የሳምንቱ ጨዋታ ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት ነው።

ሁለተኛውን ዙር በድል የጀመሩት ደቡብ ፖሊስ እና ድሬዳዋ ከተማ ነገ በ09፡00 ሀዋሳ ላይ በ17ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ይገናኛሉ። ለረጅም ሳምንታት በውጤት መዳከር ውስጥ የቆየው ደቡብ ፖሊስ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ያሳካቸው ድሎች ነጥቡን ከ5 ወደ 14 ከፍ አድርገውለት ከወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ላይ መድረስ ችሏል። ቡድኑ ከውጤት ባለፈም በራስ መተማመኑ በእጅጉ ክፍ ብሎ በተረጋጋ የኳስ ፍሰት ያለጫና የሚያጠቃ እና በፍጥነት ወደ ጎል የሚደርስ አይነት ሆኖ እየተስተዋለ ነው። ከዚህ አንፃር ነገም ወደ ድሬ የሜዳ አጋማሽ የሚያደላ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በማሳካት ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥር ቡድን ከቢጫ ለባሾቹ ይጠበቃል። የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድን ያለምንም የጉዳት እና ቅጣት ዜና ሙሉ ስብስቡን ይዞ ለጨዋታው የሚቀርብ ይሆናል።

ከአሸናፊነት በራቁባቸው አራት ጨዋታዎች የመጀመሪያውን ዙር ያገባደዱት ድሬዳዋ ከተማዎች ኢትዮጵያ ቡና ላይ ባሳኩት ድል ሁለተኛውን አጋማሽ በጥሩ መንፈስ ጀምረዋል። ከአደጋ ዞኑም በአራት ነጥቦች የራቁ ሲሆን ነገም ይህን ልዩነት ይበልጥ ለማስፋት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በርግጥ ጨዋታው ከሜዳ ውጪ እንደመደረጉ ብርቱካናማዎቹ በተለይም ግብ ካገኙ ወደ መከላከሉ ማመዘናቸው የሚቀር አይመስልም። መስመሩን ይዘው ቡድኑ በፍጥነት ወደ ማጥቃት እንዲሸጋገር የሚረዱ እንደ ገናናው ረጋሳ አይነት ተጫዋቾችም የግብ ዕሎችን ለመፍጠር ጥሩ አማራጭ መፍጠራቸው አይቀርም። ድሬዎች በጨዋታው ፍቃዱ ደነቀ እና ሳሙኤል ዮሀንስን በጉዳት የሚያጡ ሲሆን ክለቡ ቅጣት በተላለፈበት በረከት ሳሙኤል ጉዳይ ይግባኝ ቢጠይቅም ነገ የሚጠቀምበት አይመስልም። ኢታሙና ኬይሙኔም በብሔራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት አገልግሎት አይሰጥም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን እርስ በእርስ ባደረጓቸው አምስት የሊግ ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ደቡብ ፖሊስ ደግሞ አንዴ ድል ቀንቶት ሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል ፤ ሁለቱም ቡድኖች አምስት አምስት ግቦችንም አስመዝግበዋል።

– ሀዋሳ ላይ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ያደረገው ደቡብ ፖሊስ ሁለቴ ድል ሲቀናው በተቀሩት ጨዋታዎች ሽንፈቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።

– ከስምንት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች አንዴ ብቻ ድል የቀናቸው ድሬዳዋ ከተማዎች አምስት ጊዜ ደግሞ አንድ ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል። ብቸኛው ድላቸውም ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ የተመዘገበ ነው።

ዳኛ

– እስካሁን በዳኘባቸው ሁለት ጨዋታዎች ዘጠኝ የቢጫ እና አንድ የቀይ ካርዶችን የመዘዘው ዳንኤል ግርማይ ይህን ጨዋታ የመምራት ኃላፊነትን ወስዷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ሐብቴ ከድር

አናጋው ባደግ– ደስታ ጊቻሞ – አዳሙ መሀመድ – አናጋው ባደግ

ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – ብሩክ አየለ

የተሻ ግዛው – ኄኖክ አየለ – በረከት ይስሀቅ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ዘነበ ከበደ – አማረ በቀለ

ረመዳን ናስር – ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ – ሬምኬል ሎክ

ሐብታሙ ወልዴ – ዳኛቸው በቀለ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *