የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አዳማ ከተማ

የ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ጅማሮውን ሲያደርግ በአዲስአበባ ስታዲየም አዳማ ከተማን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ግብ በመታገዝ ወደ ድል የተመለሰበትን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ከጨዋታው በኋላም የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

” ተጫዋቾቻችን ላይ የነበረውን ጫና ለማስወገድ በማሸነፋችን በጣም ተደስቻለሁ” ስቴዋርት ሃል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው

“የዛሬው ድል እጅጉን ያስፈልገን ነበር ፤ ያሳለፍነው ሳምንት በጣም ከባድ ነበር። ተጫዋቾቻችን በጣም ስሜታቸው ተጎድቶ ነበር። በሳምንቱ አጋማሽ ከተጫዋቾቹ ጋር ውይይት አድርገን ተጫዋቾቹ ለውጤት ማጣታችን ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስዱና ለማሻሻል እንደሚሰሩ ተነጋግረን የዛሬውን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ እንደሚገባን ተማምነን ነበር፡፡የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፋችን ተጫዋቾቻችንን በአዕምሮ እንዲሁም በስሜት ደረጃ ለማነሳሳት እጅግ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ በጨዋታው ከውጤቱ ባሻገር በእንቅስቃሴ ደረጃ ወጣ ገባ የሚል እንቅስቃሴን አሳይተናል። ነገር ግን ተጫዋቾቻችን ላይ የነበረውን ጫና ለማስወገድ በማሸነፋችን በጣም ተደስቻለሁ፡፡”

“ደጋፊዎቻችን ላይ ከደረሰው ነገር አንጻር ጨዋታውን ማስቆም ቢገባንም የሚከተለውን ቅጣት አስበን ለመጫወት ተገደናል፡፡ ” ሲሳይ አብርሃ- አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው እንደተመለከታችሁት ብዙም ለማውራት የሚያስችል አይደለም ፤ መጀመሪያ እኛ ተጫዋች ላይ ጥፋት ተሰርቶበት ነበር፤ ዳኛው በዛ ቅፅበት ጨዋታውን ማስቆም ነበረበት። ሲቀጥል ምኞት የቡድናችን አምበል እንደመሆኑ ዳኛው ሊታገሰው ይገባ ነበር፡፡ አሁን ላይ እኔ እንደዚህ ነው ብል ጥቅም የለውም። በጉዳዩ ዙርያ አስተያየት ብሰጥ ነገ ከፍተኛ ችግር ይፈጠራል፤ ምኞት ራሱን ሆነ የቡድን አጋሮቹን ማረጋጋት ባለመቻሉ ይህ ነገር ሊፈጠር ችሏል፡፡”

በጨዋታው ይዘውት ስለገቡት እቅድና ስለ ደጋፊዎች

“እኛ አስበን የገባነው 4-3-3 ለመጫወት ነበር። በዚህም ከመከላከል ይልቅ አጥቅቶ መጫወትን ምርጫችን አድርገን ነበር የገባነው ፤ ወደዚህ ስንመጣ ማሸነፍን ተቀዳሚ ምርጫችን አድርገን ነበር። ከዛ ይልቅ ማውራት የሚገባን ከሜዳ ውጭ ስለነበረው ክስተት ነው፡፡ በጣም በሚያሳዝን መልኩ ደጋፊዎቻችን ላይ ከደረሰው ነገር አንጻር ጨዋታውን ማስቆም ይገባን ነበር። ነገርግን የሚከተለውን ቅጣት አስበን ለመጫወት ተገደናል፡፡ ብዙ ደጋፊዎቻችን ተጎድተው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *