ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል

የ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ሲጀምር አዲስ አበባ ላይ አዳማ ከተማን ያሰተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ግብ አሸንፏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ባህር ዳር አቅንቶ በሽንፈት ከተመለሰበት ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ፓትሪክ ማታሲ፣ አሲፍ ቡርሀና፣ ጋዲሳ መብራቴ እና አቤል ያለው በለዓለም ብርሀኑ ፣ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ፣ ኄኖክ አዱኛ እና ጌታነህ ከበደ ተተክተዋል። በአንፃሩ አዳማዎች ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ሱሌይማን መሐመድ እና ቀይ ካርድ የተመለከተው ብዙዓየሁ እንዳሻውን በተስፋዬ በቀለ እና ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በተመለሰው በረከት ደስታ በመለወጥ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ ፉክክር በተስተዋለበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጥሩ ጥሩ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያልታዩ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች የግብ ማግባት አማራጫቸውን ከረጃጅም ኳሶች በማድረግ ተንቀሳቅሰዋል።

በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በተመራው ጨዋታ የግብ ማግባት ሙከራ የተስተናገደው በአራተኛው ደቂቃ ሲሆን ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፍሪምፖንግ ሜንሱ አማካኝነት ያገኙትን የመዓዘን ምት አሻምተው ግብ ለማስቆጠር ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ብልጫ የተወሰደባቸው እንግዶቹ ከ14ኛው ደቂቃ በኋላ ወደ ጨዋታው በመመለስ የተወሰደባቸውን ብልጫ ወደራሳቸው ለመመለስ ጥረዋል። በዚህኛውም ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ከርቀት ያገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ መቶት ግብ ለማስቆጠር በመቃረብ የቡድኑን የመጀመሪያ ሙከራ ሰንዝሯል። ዳዋ መቶት ግብ ጠባቂው ወደ ውጪ ያጣውን ኳስ በመጠቀም የመዓዘን ምት ያገኙት አዳማዎች በደቂቃ ልዩነት በኤፍሬም ዘካሪያስ አማካኝነት ሌላ አጋጣሚ ፈጥረው መክኖባቸዋል።
የአማካይ መስመሩን ከአጥቂ መስመሩ ጋር የሚያገናኝላቸው ተጨዋች አጥተው ሲቸገሩ የነበሩት ጊዮርጊሶች ሙሉዓለም መስፍንን ወደ ፊት ጠጋ በማድረግ የተለያዩ አማራጦችን ሞክረዋል። በ17ኛው ደቂቃም ተጨዋቹ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ጌታነህ አግኝቶ ሲሞክረው ግብ ጠባቂው አምክኖበታል። አዳማዎች ላይ ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ጊዮርጊሶች ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ባገኙት የቅጣት ምት ሌላ አጋጣሚ አግኝተው ግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜ ራሱን ለጉዳት አጋልጦ አውጥቶባቸዋል።

እንደ ጊዮርጊሶች ሁሉ በፈጣሪ አማካኝ እጥረት ግብ ለማስቆጠር የተቸገሩት አዳማዎች መሃል ለመሃል ከሚደረግ የማጥቃት ሂደት ይልቅ የመስመር ጥቃት ለመሰንዘር ሞክረዋል። በንፅፅር የተሻሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ በ36ኛው ደቂቃ በተሞከረ ሌላ ጥሩ ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በዚህኛው ደቂቃ በግራ መስመር ተሰልፎ የነበረው ሪቻርድ አርተር ወደ ቀኝ መስመር በመሳብ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ የመታው ኳስ ፊት ለፊት በመሆኑ ግብ ጠባቂው ይዞበታል።

እንደ ጅማሮው ተቀዛቅዞ ያልተጠናቀቀው ጨዋታው በተለይ በመጨረሻዎቹ የመጀሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን አስመልክቷል። በ42ኛው ደቂቃ ኤፍሬም በተከላካዮች መሃል ለበረከት አመቻችቶ በመከነው ኳስ አዳማዎች መሪ ሆነው ወደ እረፍት ሊያመሩ የሚችሉበት እድል ሲያመክኑ ጊዮርጊሶች ደግሞ በ44ኛው ደቂቃ በተፈጠረ የሙሉዓለም የግምባር ኳስ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት የተሻለ የሜዳ ላይ ፉክክር ሲታይ በተለይ ባለሜዳዎቹ ጊዮርጊሶች ተጭነው ለመጫወት ሲጥሩ ተስተውሏል። በ50ኛው ደቂቃም ፈረሰኞቹ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው በኃይሉ አሰፋ የቅጣት ምት ገና በጅማሮው ግብ ለማስቆጠር ጥረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ለዓለም ብርሀኑ የመታውን ኳስ ግዙፉ የአዳማዎች ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ በግምባሩ ለመመለስ ሞክሮ ሲያመልጠው ጌታነህ አግኝቶት ለመጠቀም ሲጥር ሌላኛው ተከላካይ ምኞት ደበበ ታግሎ ኳሷን አውጥቷታል።

የአማካይ ስፍራ ጥምረታቸውን ለማስተካከል የሞከሩት አዳማዎች በ62ኛው ደቂቃ ቀይረው ወደ ሜዳ ባስገቡት ፉአድ ፈረጃ ታጋይነት ጥሩ እድል ፈጥረዋል። ፉአድ ከናትናኤል ዘለቀ ጋር ታግሎ ለዳዋ ያቀበለውን ኳስ ዳዋ ወደ ግብ የመታት ሲሆን ኳሷ በግብ ጠባቂው ትይዮ በመሄዷ መክናለች። ለዚህኛው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ጊዮርጊሶች ከሁለት ደቂቃ በኋላ ጥቃት ሰንዝረዋል። ሐምፍሬይ ሜዬኖ ያመቻቸለትን ኳስ ሳይጠቀም የቀረው ጌታነህ የመታው ኳስ ብዙም ሃይል ስላልነበረው በግብ ጠባቂው ቁጥጥር ስር ውሏል።

ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ እድል የፈጠሩት ጊዮርጊሶች ጌታነህ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ በተገኘ ቅጣት ምት ግብ ለማስቆጠር ጥረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ይህ የቅጣት ምት እንዲገኝ ጥፋት ሰርቶ የነበረው የአዳማዎች አምበል ምኞት ደበበ ከሁለተኛ ደቂቃዎች በኋላ ሁለተኛ ቢጫ በመመልከቱ ከጨዋታው ተሰናብቷል። በ77ኛው ደቂቃም የተሰራባቸውን ጥፋት ተከትሎ የቅጣት ምት ያገኙት ፈረሰኞቹ አጋጣሚውን በጌታነህ አማካኝነት ሞክረው ግብ ጠባቂው አክሽፎባቸዋል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ ከጨዋታ ውጪ ነው በማለት የተዘናጉት የአዳማን ተከላካዮችን በማዘናጋት አምልጦ የወጣው አቤል ያለው ለጌታነህ ከበደ ጥሩ ኳስ አመቻችቶለት ጊዮርጊሶች ግብ አስቆጥረዋል።

በግቡ መቆጠር ደስተኛ ያልሆኑት አዳማዎች በ84ኛው ደቂቃ ግቡ የተቆጠረበት መንገድ ልክ አይደለም በማለት ክስ አስይዘዋል። ምኞት ደበበ በቀይ ካርድ ከወጣበት ሰዓት አንስቶ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች ግቡ የተቆጠረበት መንገድ ላይ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በፈጠሩት ግጭት በርካታ ደጋፊዎች ተጎድተዋል። ይህን ተከትሎም ሙሉ ለሙሉ ስታድየሙን ለቀው ወጥተዋል።

ክስ ለማስያዝ ስድስት ደቂቃዎች የተቋረጠው ጨዋታው እንደ አጀማመሩ ቀዝቀዝ ያለ ጨዋታ አስመልክቶ ተጠናቋል። ጨዋታውን የመሩት የእለቱ ዳኛ በላይ ታደሰ ጨዋታው ማብቃቱን ለማመላከት ፊሽካ በሚነፉበት ቅፅበት የስታዲየሙም መብራት እኩል ጠፍቶ ጨዋታው ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ አግኝቶ ደረጃውን አሻሽሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *