የአሰልጣኞች አስተያየት | ደቡብ ፖሊስ 1-0 ድሬዳዋ ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ደቡብ ፖሊስ ሀዋሳ ላይ ድሬዳዋን አስተናግዶ በሄኖክ አየለ ግሩም የግንባር ኳስ 1-0 በሆነ ዉጤት ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“በቀጣይ ከዚህ የተሻለን ነገር ጠብቁ ” ገብረክርስቶስ ቢራራ – ደቡብ ፖሊስ

ስለ ቡድኑ ውጤታማነት

ተጫዋቹ በይበልጥ ስለተነሳሱ ከዚህ የተሻለ ነገር ጠብቁ። መውረድ የሚባል ነገር የለም፤ ጨዋታዎቹ ገና ናቸው፡፡ በግማሽ ሲዝን ዋንጫ ማሸነፍ አይቻልም፤ በተመሳሳይ በግማሽ ሲዝንም መውረድ የለም። በሁለተኛ ዙር ስድስት ነጥብን ይዘናል፡፡ ተጫዋቾቼ ስላለፈው ነገር ብዙም አያሳስባቸውም። አሁን ስላለው ነገር ብቻ ነው። ከመከላከያ ጨዋታ ዛሬ የተሻልን ነበርን፡፡ ችግሮቻችን ላይ ሰርተን የተሻለ ውጤት በቀጣይ እናመጣለን፡፡

ስለ አበባው ቀይ ካርድ

ዳኛው ቀይ ካርድ አሳይቷል። ምክንያቱ ምን እንደሆነ አላውቅም። ለኔ ሊገባኝ አልቻለም። ይህ ቀይ ካርድ የሚያሰጥ አይመስለኝም። ኳሱ ከሜዳ ውጪ ነው ያለው። ሁሉም ቆመው ነው ያሉት። በምን እንደታየ በፍፁም ይህን ነገር  መለየት አልቻልኩም።

“ስለ ዳኝነት ማውራት ሰልችቶኛል” ስምዖን ዓባይ ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው

በእንቅስቃሴ ረገድ ጎል እስከተቆጠረብን ድረስ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገን ብልጫም ወስደናል። በተለይ ሁለተኛ አጋማሽ በደንብ ብልጫ ወስደናል። ቢሆንም ግን ይሄ እግር ኳስ ነው። ልክ አበባው በቀይ ከወጣበት 1 ደቂቃ በኋላ ጎል ገባብን። የሱ መውጣት ለኛ አልጠቀመንም።

ተጫዋቾቼ ጎሉን ያልጠበቁትና ያልገመቱት ነበር። ወደ ጨዋታው ቅኝት ለመምጣት ወደ ሰባት እና ስምንት የሚሆኑ ደቂቃዎች የነበሩ ቢሆንም ለመመለስ አልቻሉም። የማልክደው ነገር  3 ነጥብ ብናጣም የተጫዋቾቼ እንቅስቃሴ የሚያስከፋ አይደለም። ጥሩ ነገር አይቻለሁ። በሚቀጥለው ያሉትን ክፍተቶች አስተካክለን የተሻለ ቡድን እንደሚኖረን እርግጠኛ ነን።

ስለ ቡድናቸው እንቅስቃሴ እና ስለ ተጋጣሚ

እግር ኳስ እንደ ተመልካቹ ነው። ሙሉ ለሙሉ ተበልጠን ነበር የሚያስብል ነገር የለም። እነሱ በተለይ ከእረፍት በፊት በኛ ሜዳ ኳስ ያንሸራሽሩ ነበር። በጥቂት ተጫዋቾች ነበር ሲንቀሳቀሱ የነበሩት። ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራም አድርገዋል። በመቶኛ ቢቀመጥ በእንቅስቃሴ የተሻሉ ነበሩ።

ስለ በረከት ቅጣት

“በመጀመሪያ በረከት ላይ የተፈፀመው ነገር ቡድናችንን ለመጉዳት ሰለሆነ ብዙም መግለፅ አልፈልግም። ሁለተኛ ኢታሙና ለብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ሀገሩ ሄዷል። ሶስተኛ በጉዳት ወሳኝ ተጫዋቾች የሉም። በ16 ተጫዋቾች ነው የገባነው። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ እንደመጫወታችን 3 ነጥብ አናግኝ እንጂ መጥፎ አይደለም። እዚህ ሊጫወት ከመጣ በኋላ በበረከት ላይ የተወሰነበት ውሳኔም መሸጋሸጎች ስላደረግን በተጫዋቾቹ  ላይ ተፅዕኖ ነበረው። እንዳያችሁት አማራጭ ስላልነበረኝ በአንድ አጥቂ ነው የተጫወትኩት።

ስለ ዳኝነት

እኔ ስለዳኝነት ማውራት ሰልችቶኛል። ማለትም መልስ ስለሌለው። በፕሪምየር ሊጉ ያሉ የ16ቱንም ክለቦች አሰልጣኞች ብትጠይቁ ተመሳሳይ መልስ ነው የሚሰጧችሁ። በዳኝነቱ ላይ መናገር አልፈልግም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply