ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ወልዋሎ እና ቡናን በሚያገናኘው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ነገ 09፡00 ላይ በትግራይ ስታድየም ከ18ኛ ሳምንት መርሀ ግብር ውስጥ አንዱ የሆነው የወልዋሎ ዓ/ዩ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ይከናወናል። በሰንጠተዡ አጋማሽ የተቀመጡት ወልዋሎዎች አራተኛ ተከታታይ ጨዋታቸውን መቐለ ላይ ያደርጋሉ። በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ስር ሁለተኛውን የውድድር አጋማሽ የጀመረው ቡድኑ የአጨዋወት እና የአሰላለፍ ለውጦችን አድርጎ መጥቷል። አምስት አማካዮችን መጠቀም የጀመሩት ወልዋሎዎች ለኳስ ቁጥጥር ቅርብ ከነበረው አቀራረባቸው ወደ ቀጥተኛ ኳሶች ያደሉ ሆነዋል። ከቡድኑ የቀኝ ክፍል በተለይም ከእንየው ካሳሁን የሚነሱ ኳሶችም በነገው ጨዋታ ለኢትዮጵያ ቡና የግራ መስመር የመከላከል ወገን ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ። ወልዋሎዎች የብርሀኑ ቦጋለን ግልጋሎት ከቅጣት መልስ የሚያገኙ ሲሆን ደስታ ደሙም ከኦሊምፒክ ቡድኑ ይመለስላቸዋል። አስራት መገርሳ ግን ከጉዳቱ ባለማገገሙ ከጨዋታው ውጪ ሆኗል።

አምስት ተስተካካይ ሽንፈቶች ከዋንጫ ፉክክሩ አርቀው ወደ አስረኛ ደረጃ ያወረዷቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች የራስ መተማመን መንፈሳቸውን ለመመለስ ከሜዳ ውጪ አሸንፎ የመመለስ ፈተና ይጠብቃቸዋል። በንፅፅር ቀላል የሆነው በሊጉ ግርጌ የሚገኘው ደደቢትን ሊገጥሙ ይችሉ የነበሩበት የሳምንቱ ጨዋታ በመተላለፉም ከድሬዳዋው ሽንፈት በኋላ ዳግም ከመዲናዋ ለመውጣት ተገደዋል። ከአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ስንብት በኋላም የቅርፅ ለውጥ ሳያደርግ በቀጠለው ቡድን ውስጥ የአማኑኤል ዮሀንስ እና አቡበከር ናስር ከኦሊምፒክ ቡድኑ የሳምሶን ጥላሁን ደግሞ ከጉዳት መመለስ ለነገው ጨዋታ መልካም ዜና ሲሆን ክሪዝስቶም ንታንቢ እና ሀሰን ሻቫኒም ከብሔራዊ ቡድን ምርጫ መልስ በድኑን ያገለግላሉ። በመሆኑም ከተመስገን ካስትሮ እና ሚኪያስ መኮንን ሌላ አዲስ ጉዳት በቡድኑ ውስጥ አልተመዘገበም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በመሸናነፍ ከተጠናቀቁት ሦስቱ የቡድኖቹ እርስ በርስ ግንኙነቶች ውስጥ ወልዋሎ ዓ/ዩ ሜዳው ላይ ቡናን 1-0 ሲረታ ኢትዮጵያ ቡና አምና እና ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ የ 2-1 እና 1-0 ድል አስመዝግቧል።

– በትግራይ ስታድየም አስር ጨዋታዎች ያደረገው ወልዋሎ አራቱን በተመሳሳይ የ1-0 ውጤቶች ሲያሸንፍ አራት የአቻ እና ሁለት የሽንፈት ውጤቶች ገጥመውታል።

– ስድስት ጊዜ ከአዲስ አበባ ስታድየም ውጪ ጨዋታዎችን ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና አንድ ድል እና ሁለት የአቻ ውጤት ሲያስመዘግብ ሦስት ጊዜ ተሸንፏል።

ዳኛ

-ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ለጨዋታው የተመደበ አርቢትር ነው። ቴዎድሮስ እስካሁን በሰባት ጨዋታዎች 27 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ ሁለት ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ ያሰናበተ ሲሆን አንድ የፍፁም ቅጣት ምትም ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ ዓ/ዩ

በረከት አማረ

እንየው ካሳሁን – ቢኒያም ሲራጅ – ደስታ ደሙ – ብርሀኑ ቦጋለ

ብርሃኑ አሻሞ – አማኑኤል ጎበና

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – አብዱርሀማን ፉሴይኒ – ኤፍሬም አሻሞ

ክርስቶፈር ችዞባ

ኢትዮጵያ ቡና (4-4-2 ዳይመንድ)

ዋቴንጋ ኢስማ

አህመድ ረሺድ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ቶማስ ስምረቱ – እያሱ ታምሩ

አማኑኤል ዮሀንስ

ሳምሶን ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ካሉሻ አልሀሰን

ሁሴን ሻቫኒ – አቡበከር ናስር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *