አስተያየቶች| ኢትዮጵያ 3-2 ዩጋንዳ

በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ቅድመ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአዲስ አበባ ስታድየም የዮጋንዳ አቻውን አስተናግዶ 3-2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች እና አምበሎች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

” ከተቆጠሩብን ሁለት ግቦች ይልቅ ይበልጥ ትኩረትን የሚስቡት ያስቆጠርናቸው ሦስት ግቦች ናቸው” አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ – ኢትዮጵያ

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች ከባድ ነበር። በመጀመሪያ 45 የተሻለ መንቀሳቀስ ብንችልም ግቦችን ማስቆጠር አልቻልንም። በሁለተኛው አጋማሽ ክፍተቶቻችን አርመን ብንገባም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታውን ጨርሰናል ብለን በማሰብ ትኩረት በማጣታችን ግቦች አስተናግደናል፤ ወደ ዮጋንዳ የምንሄደው ግን ለማሸነፍ ነው፡፡”

ስለ መስመር ተከላካዮች ደካማ የማጥቃት ተሳትፎ እና ስለሲናፍ ተደጋጋሚ ስህተቶች

“ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ከኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ ማነስ የተነሳ በማጥቃቱ እምብዛም ሲሳተፉ አልታየም ፤ ይህን በቀጣይ ጨዋታ ቀርፈን ለመግባት እንጥራለን፡፡ የሲናፍ አጨዋወት ኳስን እየገፉ በመሄድ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህንን እንዳታደርግ ብንከለክላት ሙሉ ለሙሉ ከጨዋታው ትጠፋለች፡፡ ስለዚህም ኳስ እየገፋች በመሄዷ ከምታጓዳው ይልቅ ጥቅሙ ስለሚያመዝን ያንን እያደረገች እንድትቀጥል ወስነናል፡፡”

በመጨረሻ ደቂቃዎች ትኩረት ስለማጣትና የጨዋታ ፍጥነትን ስለመቆጣጠር

“በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩብን ግቦች ውጤቱ ሊጠብ ችሏል፡፡ ለእኔ እንደ አሰልጣኝ ከተቆጠሩብን ሁለት ግቦች ይልቅ ይበልጥ ትኩረትን የሚስቡት ያስቆጠርናቸው ሦስት ግቦች ናቸው፡፡ በቀጣይ የተጫዋቾቻችን የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ እየዳበረ ሲሄድ መሠል የመጨረሻ ደቂቃዎች የትኩረት ማጣት ችግሮችን እየቀረፍን ለመሄድ እንጥራለት፡፡የጨዋታን ፍጥነት በመቆጣጠር በኩል ክፍተቶች እንዳሉ አስተውለናል ፤ በእኔ የአጨዋወት መንገድ በአጭር ኳስ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል እንድንሄድ እፈልጋለሁ ፤ ተጫዋቾቼ የእኔን አጨዋወት በመጀመሪያ ጨዋታዎች ለመተግበር የተቻላቻውን ስላደረጉ ሊመሠገኑ ይገባል፤ በማፈጥኑም ሆነ ማረጋጋት በሚገባቸው ጊዜ ክፍተቶች ቢኖሩም በቀጣይ ለማረም እንሰራለን፡፡”

ብርቱካን ገ/ክርስቶስ – አምበል

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው ፉክክር የበዛበት ነበር፤ ያገኘናቸውን በርካታ አጋጣሚዎች መጠቀም አለመቻላችን የሚያስቆጭ ቢሆንም ሶስት ግቦችን ማስቆጠር ችለናል ነገር ግን በትኩረት ማጣት ለዚህ ውጤት ተዳረግን እንጂ ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡”

” በመጨረሻ ደቂቃ የተቆጠሩት ግቦች ለእኛ በጣም ጠቃሚ ናቸው” – አሰልጣኝ ቡሌጋ ፋሪዳህ – ዩጋንዳ

በመጨረሻ ደቂቃ የተቆጠሩት ግቦች በመልሱ ጨዋታ ስለሚኖራቸው አንድምታ

“በመጨረሻ ደቂቃ የተቆጠሩት ግቦች ለእኛ በጣም ጠቃሚ ናቸው፡፡ ለመልሱ ጨዋታ ሁለቱ ግቦች ሞራላችን በማነሳሳት በኩል ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል ፤ አንድ ግብ ማስቆጠር ከቻልን አላፊ ስለምንሆን ግቦቹ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል፡፡”

አቶሮ ሩት – አምበል

ስለ ጨዋታው

” ከሜዳ ውጪ እንደሚጫወት ቡድን ጨዋታው ቀላል የሚባል አልነበረም ፤ ሁለቱም ቡድኖች ለማሸነፍ የተቻላቸውን አድርገዋል፡፡ እኛም ከኋሏ ተነስተን ሁለቱን ግቦች ለማስቆጠር የተቻለንን ጥረናል፡፡ ቡድናችን ተስፋ ሰጪ ነገር አሳይቷል በሜዳችን እንደምናሸንፍ በቡድናችን ሙሉ እምነት አለኝ ምክንያቱም በዚህ ድካም ውስጥ ሆነን ይህንን ማድረግ ከቻልን በሜዳችን ደግሞ ከዛሬው የተሻለ ነገር መስራት እንችላለን፡፡”

ስላስተናገዷቸው ሦስቱ ግቦች

” ተከላካይ መስመራችን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አልነበረም ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ግን መሻሻሎች ነበሩ፡፡በሁለተኛው አጋማሽ ያስገባናቸው አጥቂዎች የቡድኑን መነሳሳት ከፍ አድርገውት በተሻለ ተጭነን መጫወት ችለናል፡፡ እንደ አጠቃላይ በመጀመሪያው አጋማሽ በራሳችን ላይ ያስቆጠርናት ግብ አጠቃላይ የመከላከል አወቃቀራችን ላይ ጫና አዛብቶብን ነበር፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: Content is protected !!