ሪፖርት | ሉሲዎቹ ዩጋንዳን በማሸነፍ ወደ ቀጣይ የኦሊምፒክ ማጣርያ ዙር አለፉ

ጃፓን በ2020 ለምታስተናግደው የኦሊምፒክ ውድድር ለማለፍ በሴቶች እግርኳስ የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ የሚገኙት ሉሲዎቹ ዩጋንዳን በድምር ውጤት 4ለ2 በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር አልፈዋል።

በካምፓላ ከተማ በሚገኘው ፊሊፕ ኦሞንዲ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ከሜዳቸው ውጪ የተወሰደባቸውን የጨዋታ የበላይነት ለመገልበጥ ጠንክረው ሲጫወቱ ተጋባዦቹ ደግሞ ከሶስት ቀናት በፊት ያገኙትን ውጤት ለማስጠበቅ ተንቀሳቅሰዋል።

አሰልጣኝ ሠላም ዘርይም ረቡዕ ዕለት ከተጠቀሙባቸው የተጫዋች ስብስብ ታሪኳ ደቢሶ፣ ዓለምነሽ ገረመው እና ሰናይት ቦጋለን በመሰሉ አበራ፣ ናርዶስ ጌትነት እና ህይወት ደንጊሶ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል። የዩጋንዳዋ አሰልጣኝ ቡሌጋ ፋሪዳህ ደግሞ ኑቡምባ ፊዮና፣ ናኑጊያ ሻምራ፣ ናቡዬትሜ ሳንድራ፣ ማቱዞ ሊላም እና ሃሙሌም ዛይማህን በማሳረፍ አኪሮር ትሬሲ፣ ናንዚሪ ሬስቲ፣ ኢካፑት ፋዚላ፣ ናሱና አሲፋህ እና ማኢምባ ፋውዚያ ወደ ሜዳ አስገብተዋል።

ገና በጨዋታው ጅማሮ ወደ ኢትዮጵያኖች የግብ ክልል በመድረስ ጥቃት መሰንዘራቸውን የጀመሩት ዩጋንዳዎች በ9ኛው እና በ10ኛው ደቂቃ ናንዚሪ ሬስቲ በሞከረቻቸው ሁለት ሙከራዎች ወደ ግብ ቀርበው ነበረ። ወደ ጨዋታው ቀስ በቀስ መግባት የቻሉት የአሰልጣኝ ሰላም ተጨዋቾች ሴናፍ ዋቁማ በ20ኛው ደቂቃ ከርቀት በመታችው ኳስ ግብ ለማስቆጠር ጥረው አቱሮ ሩት አምክናባቸዋለች። ባለሜዳዎቹ ዩጋንዳዎች በጨዋታው ግብ ለማስቆጠር አሁንም ጥረታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በ34ኛው ደቂቃ በተሞከረ የቅጣት ምት በድጋሜ ወደ ግብ ቀርበው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ዳግም የኢትዮጵያን ግብ ለመፈተሽ የጣሩት ዩጋንዳዎች ኢኩዋፑት ፋዚላ በሞከረችው ነገር ግን የግቡ ቋሚ በመለሰው ሙከራ ይበልጥ ግብ ለማስቆጠር ከጫፍ ደርሰው ነበር።

ከእረፍት መልስ ተከታታይ ለውጦችን አድርገው የተጫወቱት ባለሜዳዎቹ ዩጋንዳዎች ወደ ቀጣይ ዙር ሊያሳልፋቸው የሚችለውን አንድ ግብ ለማስቆጠር በመጠኑ ተጭነው ተጫውተዋል። ነገር ግን ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተጠናክረው ወደ ሜዳ የገቡት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ተረጋግተው በመጫወት በመጀመሪያው አጋማሽ የተወሰደባቸውን የጨዋታ ብልጫ ለማስመለስ በመንቀሳቀስ ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። ሰርካዲስ ጉታ ወደ ጎል የመታችው ኳስ ተጨራርፎ እግሯ ላይ የደረሰታ ሎዛ አበራ በ66ኛው ደቂቃ አጋጣሚውን ወደ ጎልነት ቀይራ ኢትዮጵያ መምራት ጀምራለች።

ሳይጠበቅ መሪ የሆኑት የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ዩጋንዳዎች ሲሰነዝሩት የነበረውን ጥቃት ለመመከት በጥብቅ መከላከል ለመጫወት ሞክረዋል። በዚህም የአጥቂ ባህሪ ያላተረ ሰርካዲስን በመቀየር የመከላከል ባህሪ ያላት ታሪኳን በማስገባት ግብ እንዳይቆጠርባቸው ጥረዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የኢትዮጵያን የተከላካይ መስመር ጥሰው መግባት የተሳናቸው ዩጋንዳዎች ጥርት ያለ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታው ተጠናቋል።

በድምር ውጤት 4ለ2 ዩጋንዳን ያሸነፉት ሉሲዎቹ በሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ካሜሩንን ነሃሴ 19 ይገጥማሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: