ሪፖርት | ቡና እና ፋሲል ያለግብ ተለያይተዋል

ተጠባቂ በነበረው የ19ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ የተገናኙት ኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ 0-0 በሆነ ውጤት ነጥብ ተጋርተዋል።
በተስተካካይ ጨዋታ ባሳለፍነው ሳምንት ደደቢትን መርታት ችለው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ካሉሻ አልሀሰንን በማሳረፍ ሳምሶን ጥላሁንን የተጠቀሙበትን ቅያሪ ብቻ ያደረጉ ሲሆን በፋሲል በኩል ደግሞ ሁለት ለውጦች ተደርገዋል። መቐለን ከረታው የዐፄዎቹ ቡድን ውስጥ በሰለሞን ሐብቴ እና ጉዳት በገጠመው ኤፍሬም ዓለሙ ምትክ ሰዒድ ሁሴን እና በዛብህ መለዮ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቹንም ከሦስት ወደ አራት ከፍ አድርጓል።

ቀደም ብሎ በጣለው ቀለል ያለ ዝናብ የተሻለ ምቾት ላይ በተገኘው ሜዳ ላይ ጨዋታው በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ጠንካራ ፉክክር ማስተናገድ ችሏል። ከጅምሩ በኳስ ቁጥጥሩ የበላይ መሆን ያልከበዳቸው ፋሲሎች በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ በመቆየት ቅብብሎችን መከወን የቻሉ ሲሆን ወደ ግብ በቀረቡበት አጋጣሚም 7ኛው ደቂቃ ላይ ከሽመክት ጉግሳ በተነሳ ኳስ በዛብህ መለዮ ለሰዒድ ሁሴን ሰጥቶት የመስመር ተከላካዩ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል። በሂደት የሱራፌል ዳኛቸው እና የበዛብህ መለዮን ጥምረት መቆጣጠር የቻሉት ቡናዎች ኳስን በእግራቸው ስር ማቆየት ባይችሉም በፈጣን ጥቃት በሁለቱ መስመሮች ደጋግመው መግባት ችለዋል። 10ኛው ደቂቃ ላይ እያሱ ታምሩ ከግራ መስመር ያሻማው ኳስ ወደ ግብ አምርቶ በሳማኬ ጥረት ሲከሽፍ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ቡናዎች አህመድ ረሺድ ካቋረጠው ኳስ ሳጥን ውስጥ በብዛት ተገኝተው ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

በተመጣጠነ አኳኋን በቀጠለው ጨዋታ ቡናዎች 17ኛው ደቂቃ ላይ ሁሴን ሻባኒ ከሳምሶን ጥላሁን ተቀብሎ ሳጥን ውስጥ አየር ላይ ባደረገው አደገኛ ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ጨዋታው ከ20ኛው ደቂቃ ካለፈ በኋላ ግን የሜዳ ላይ ግጭቶች ተበራክተው ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ለጉዳት ይጋለጡ ነበር። በዚህም ኢትዮጵያ ቡና አምበሉ አማኑኤል ዮሐንስን ወደማብቂያው ላይ ደግሞ ክሪዚስቶም ንታንቢን ቀይሮ ለማስወጣት ተገዷል። የፋሲሎች ጥቃት ጋብ ባለባቸው በነዚህ ጊዜያት በሽመክት እና ኢዙ አዙካ በኩል ለመግባት ጥረት ቢያደርጉም የፊት አጥቂው መጂብ እንቅስቃሴ በመጠኑ መጉላት ጀምሮ ነበር። ሙጂብ 32ኛው ደቂቃ ላይ ከሱራፌል የተቀበለውን ኳስ ከተከላካዮች ታግሎ በመግባት ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራም ተጠቃሽ ነበር። በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል ደግሞ አማኑኤልን ቀይሮ የገባው ካሉሻ አልሀሰን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ለማድረስ የሚያደርገው ጥረት በተደጋጋሚ ይታይ የነበረ ቢሆንም ግልፅ የማግባት ዕድል መፍጠር ሳይችል ጨዋታው ወደ እረፍት አምርቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ በአመዛኙ የፋሲሎች የበላይነት የታየበት እና በርካታ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ተደርገው ለማመን በሚከብድ መልኩ የተሳቱበት ነበር። በተሻለ ሁኔታ ጫና ፈጥረው በመጫወት ከዕረፍት የተመለሱት ቡናዎች 55ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን እና አቡበከር ከፈጠሩት ቅብብል አቡበከር ያደረገውን ቀላል ሙከራ ብቻ መፍጠር ችለው ነበር። ጨዋታው በተሻለ ፍጥነት ሲቀጥልም ሀለቱም ቡድኖች ወደ ፊት ከደረሱ በኋላ ባልተመጠኑ ቅብብሎች ጥቃቶቻቸው ሲበላሹ ይታይ ነበር። በፋሲሎች በኩል ከሳጥን ውጪ ይደረጉ የነበሩ ሙከራዎች በብዛት ሲታዩ 57ኛው ደቂቃ ሙጂብ ድንቅ ሆኔ ካመሸው ሽመክት ጉግሳ በተላከለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ዕድሉን ሳይጠቀም ቀርቷል።

60ኛው ደቂቃ ላይ ዓለምብርሀን ይግዛውን በኢዙ አዙካ ቀይረው ያስገቡት ፋሲሎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ከፍተኛ ብልጫን በማግኘት ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ አምሽተዋል። በተለይም ቡድኑ የሜዳውን የጎን ስፋት በመጠቀም በተጋጣሚው የተከላካይ መስመር ግራ እና ቀኝ ሰፋፊ ክፍተቶችን በመፍጠር ከመሀል በሚሰነጠቁ ኳሶች ወንድወሰንን በተደጋጋሚ ፈትኗል። ጉልበት ያጣው የቡና የአማካይ ክፍልም ቅብብሎቹን ማቋረጥ ተስኖት ለተደጋጋሚ ጥቃት እንዲጋለጥ ሆኗል። 64ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ከግራ ወደ ሳጥን ውስጥ ፤ 83ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሽመክት በተከላካዮች መሀል ባደረሱት ኳስ ያለቀላቸው ዕድሎች ያገኘው ዓለምብርሀን ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል። 84ኛው ደቂቃ ላይም ሽመክት ከሱራፌል የተቀበለውን ኳስ ሳጥን ውስጥ አክርሮ መትቶ ወንድወሰን ይዞበታል። ከነዚህ ከባድ ሙከራዎች ግብ ያልተቆጠረባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻለ ሙከራ ያደረጉት በጭማሪ ደቂቃ ካሉሻ ከማዕዘን ምት በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ በወጣበት ኳስ ነበር።

ጨዋታው እጅግ ፈጣን በሆነ እና በሙከራዎች በታጀበ እንቅስቃሴ በቀጠለባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች የተፈጠሩ ክስተቶች በዕለቱ ኢንተርናሽናል አርቢትር በዓምላክ ተሰማ ላይ ተቃውሞዎችን የጋበዙ ሲሆን በተለይም ዓለምብርሀን ወደ ሳጥን ይዞ በገባው የመልሶ ማጥቃት ኳስ እያሱ ታምሩ ለማስጣል ባደረገው ጥረት የተነሳው የፋሲሎች የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄ በይበልጥ ትኩረትን ያሳበ ነበር።

በብዙው የተጠበቀው ጨዋታ ያለግብ ሲጠናቀቅም ሁለቱም ቡድኖች በነበሩበት ደረጃ ላይ እንዲቆዩ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡