ሪፖርት| መቐለ ከሁለት ተከታታይ ጨዋታ ነጥብ መጣል በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

ምዓም አናብስት በአማኑኤል ገ/ሚካኤል ብቸኛ ግብ ወላይታ ድቻን በማሸነፍ ከተከታዮቻቸው ያላቸው ልዩነት ማስጠበቅ ችለዋል።

ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ባለፈው ሳምንት በፋሲል ሽንፈት ከደረሰበት ስብስባቸው በአንተነህ ገብረክርስቶስ እና ኦሴይ ማውሊ ምትክ ሄኖክ ኢሳይያስ እና ያሬድ ብርሃኑ ወደ ቋሚ አሰላለፍ አካተው ጨዋታውም ሲጀምሩ የጦና ንቦች በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንት ሃዋሳን ካሸነፈው ስብስባቸው ውብሸት ዓለማየሁ፣ ሄኖክ አርፊጮ እና እዮብ ዓለማዮህ ሲያስወጡ በምትካቸው አንተነህ ጉግሳ ፣ አወል ዓብደላ እና ፀጋዬ አበራ አካተው ጨዋታው ጀምረዋል።

በእንግዶቹ ፍፁም ብልጫ የጀመረው ጨዋታው በመጀመርያው አጋማሽ ብርቱ ፉክክር እና በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች የታየበት ሲሆን ባለሜዳዎቹ መቐለዎች በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ከመውሰድ አልፈው ጠንካራውን እና በርካታ ተጫዋቾች የሚያሳትፈውን የወላይታ ድቻ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው የግብ ዕድል የፈጠሩበት አጋጣሚ ጥቂት ነበር። እሸቱ መና ከቅጣት ምት ባደረጋት ሙከራ የመቐለን ግብ መፈተሽ የጀመሩት የጦና ንቦች ለተጋጣሚ ፈታኝ በነበረው በፈጣኑ የማጥቃት ሽግግራቸው ተጠቅመው በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል በተለይም አላዛር ፋሲካ የአሚን ነስሩን ስህተት ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ተገናኝንቶ ያመከነው እና ባየ ገዛኸኝ ተጫዋቾች አልፎ መቶ አሌክስ ተሰማ ተደርቦ ያወጣው የጦና ንቦች ካመከኗቸው ወርቃማ ዕድሎች ይጠቀሳሉ።

በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች በተጨማሪም በዓብዱልሰመድ ዓሊ እና በባዬ ገዛኸኝ ጥሩ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ባየ ገዛኸኝ ከቸርነት ጉግሳ በጥሩ ሁኔታ የተሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ ያልተጠቀመበት ዕድል በጦና ንቦች የተሞከረው ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር። ከዚህ ውጭ አላዛር ፋሲካ ባየ ገዛኸኝ በግሉ ጥረት ወደ መቐለ ሳጥን ገብቶ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ መቶ ፍሊፕ ኦቮኖ ያዳነው ኳስም ይጠቀሳል።

በመጀመርያው አጋማሽ ከ ኳስ ቁጥጥር ብልጫ ባለፈ ንፁህ የግብ ዕድሎች ሲፈጥሩ ያልታዩት ምዓም አናብስትም ምንም እንኳ እንደ ተጋጣያቸው ንፁህ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ባያደርጉም ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች አድርገው ነበር። ከነዚህም ሃይደር ሸረፋ እና ያሬድ ብርሃኑ በጥሩ ቅብብል ገብተው ሃይደር ከ ሳጥኑ ጠርዝ አከባቢ አሻምቷት አማኑኤል ከማግኘቱ በፊት ደጉ ደበበ ያወጣት እና ያሬድ ብርሃኑ አማኑኤል ገብረሚካኤል ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ገጭቶ ያደረጋት ሙከራ ይጠቀሳሉ።

መቐለዎች ከነዚ ሙከራዎች ውጭም የመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻ ደቂቃ ላይ የፈጠሯት ዕድል የተሻለ ለግብ የቀረበች ነበረች። አማኑኤል ከሚካኤል ደስታ የተሻማውን የመዓዝን ኳስ በግንባሩ ሲገጭ በቅርበት የነበረው አብዱልሰመድ ዓሊ ተደርቦ መልሷታል።

መቐለዎች ብልጫ ወስደው የተጫወቱበት እንዲሁም በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ የተንቀሳቀሱት የጦና ንቦች ወርደው የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ አስገራሚ የታክቲክ ለውጥ የታየበትም ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ በአራት ተከላካይ ወደ ሜዳ የገቡት መቐለዎች በሁለተኛው አጋማሽ ቢያድግልኝ ኤልያስ በዮናስ ገረመው ቀይረው በማስገባት ካለ ተፈጥሯዊ የመስመር ተጫዋች (Wing Back) ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። በዚህም ጋብርኤል አህመድ እና ያሬድ ከበደ ወደ ሁለቱም መስመሮች አጋድለው እንዲጫወቱ ተደርጓል። ጥቂት የግብ ሙከራዎች በታየበት አጋማሽ ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማድረግ ቅድምያ የያዙት ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ሲሆኑ ያሬድ ከበደ ከአማኑኤል የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ መትቶ ታሪኬ ጌትነት መልሶበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ካሳዩት ጥሩ የመከላከል ቅርፅ ውጭ ይህ ነው የሚባል ጥሩ የማጥቃት አጨዋወት ሲተገብሩ ያልታዩት የጦና ንቦች በ አላዛር እና ባየ ጥሩ ዕድሎች ፈጥረው ነበር በተለይም ባየ በጥሩ ብቃት በመስመር ይዞ ገብቶ አሻምቶት አሚን ነስሩ እንደምንም በግንባሩ ገጭቶ ያወጣው ጥሩ ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት ግብ ለማስቆጠር ተጭነው የተጫወቱት መቐለዎች በሰባ አራተኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ሰምሮ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ ተነክታለች በሚል የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ዋና ዳኛው እና አምበሉ ደጉ ደበበ ካደረጉት ከረጅም ደቂቃ የወሰደ ክርክር በኃላ ነበር አጥቂው አማኑኤል መቶ ያስቆጠረው።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ያላሳዩት ወላይታ ድቻዎች በአብዱልሰመድ ዓሊ እና ባየ ገዛኸኝ ሙከዎች ቢያደርጉም አቻ የምታደርጋቸው ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በአንፃሩ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር አጥቅተው የተጫወቱት መቐለዎች በመጨረሻው ደቂቃ መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ የሚያደርጉበት ዕድል አግኝተው ነበር ፤ ሳሙኤል ሳሊሶ ከዮናስ ገረመው የተላከለት ኳስ ከ ታሪኬ ጌትነት አንድ ለ አንድ ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው በድንቅ ብቃት አምክኖታል።

ውጤቱ በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ መቐለ ከተከታዮቹ ያለውን ልዩነት ማስጠበቅ ሲችል ወላይታ ድቻ ከአራት ጨዋታ በኋላ ሽንፈት ገጥሞታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡