ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

የአዳማ እና ሀዋሳ ጨዋታን የተመለከቱ ነጥቦች እነሆ…

ከሊጉ ወገብ ዝቅ ብለው በዕኩል 26 ነጥቦች ተከታታይ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ እና አዳማ ነገ 09፡00 ላይ በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታድየም ይገናኛሉ። ባለሜዳው አዳማ ከተማ ከአሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀ ጋር ከተለያየ በኋላ የሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ ነው። በሁለተኛው ዙር ሽረን ከረቱበት ጨዋታ ውጪ ሌላ ድል ያላገኙት አዳማዎች 10ኛ ሆነው ተቀምጠዋል። ሳምንት ሲዳማ ላይ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላም ነበር ከአሰልጣኛቸው ጋር ለመለያየት የወሰኑት። እንደወትሮው ሁሉ ከባድ ፉክክር እንደሚደረግበት በሚጠበቀው የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት አዳማዎች አሁንም አጥቂያቸውን የማያገኙ በመሆኑ ለከነዓን በሰጠት አዲስ ሚና እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል። ለኳስ ቁጥጥር እና ከመስመር ለሚነሱ ጥቃቶች ምቹ በሆነው የአማካይ መስመራቸው ላይ በመመስረትም ከሀዋሳ ሦስት ተከላካዬች ግራ እና ቀኝ ባሉት ቦታዎች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ይመስላል። በሀሰተኛ አጥቂነት ሚና ከፊት ሊሰለፍ የሚችለው ከነዓን ከአማካዮቹ ጋር በሚኖረው የቅብብል ግንኙነት ከሀዋሳ ተከላካይ አማካዮች ጋር የሚገናኙባቸው ቅፅበቶችም ተጠባቂ ናቸው ። አዳማ አሁንም ያላገገመው አንዳርጋቸው ይላቅ እና ዳዋ ሆቴሳን በጉዳት ቡዙዓየሁ እንዳሻውን ደግሞ በቅጣት ሲያጣ ቡልቻ ሹራ ግን ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ ወደ ሜዳ በነገው ጨዋታ ሊመለስ እንደሚችል ይገመታል።

በመጀመሪያው ዙር ከነበረው የፉክክር ደረጃ እጅግ የወረደው ሀዋሳ ከተማ በአንፃራዊነት ጠንካራ ሆኖ በሚታይበት ሜዳው ላይ ሙሉ ነጥቦችን ሳያገኝ ከባህር ዳር አቻ ተለያይቶ ነው ወደ አዳማ የሚያቀናው። ሁለተኛው ዙር ከገባ ሁለት ነጥቦችን ብቻ ያሳኩት ሀዋሳዎች ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በሙሉም ግብ ተቆጥሮባቸዋል። ይህም በመጨረሻ የሜዳው ጨዋታ ላይ አራት ግቦችን ካስመዘገበው ተጋጣሚያቸው አንፃር ስጋት ላይ የሚጥላቸው ጉዳይ ነው። በማጥቃቱም ቢሆን ቡድኑ እንደመጀመሪያው ዙር ከመስመር ተመላላሾቹ የሚነሱ ኳሶች በአጥቂዎች ወደ ግብ የሚቀይርበት ንፃሬ እየቀነሰ ነው። በነገውም ጨዋታ ሌላኛው የቡድኑ አማራጭ የሆኑት ከታፈሰ ሰለሞን የሚነሱ ኳሶችም ሲታሰቡ ከአዳማ የአማካይ ክፍል አንፃር ተጨዋቹ በቂ ሽፋን ካላገኘ ልዩነት የሚፈጥሩበት ዕድል ሰፊ ላይሆን ይችላል። አዲስዓለም ተስፋዬ እና ፍቅረእየሱስ ተወልደብርሃንን በቅጣት ገብረመስቀል ዱባለን በጉዳት ሳቢያ ያልያዙት ሀዋሳዎች ምንአልባትም የመስመር ተመላላሾቻቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ቀነስ አድርገው ወደ ቀጥተኛ ኳሶች የሚያደላ ዕቅድ ይዘው እንደሚገቡም ይገመታል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች አስካሁን 36 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ 17 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ በግማሽ አንሶ 8 ጊዜ ድል አድርጓል፡፡ በ11 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ሀዋሳ 42 ጎሎች ሲያስቆጠር አዳማ ከተማ 35 አስቆጥሯል፡፡

– አዳማ ከተማ በሜዳው ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት እና ሦስት የአቻ ውጤትን ሲያስመዘግብ አምስት ጨዋታዎችን በድል መወጣት ችሏል።

– ከሜዳው ውጪ አንድ ድል ብቻ ማስመዝገብ የቻለው ሀዋሳ ከተማ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲሸነፍ ሦስቴ ነጥብ መጋራት ችሏል።

ዳኛ

– አዳማን ከደቡብ ፖሊስ እና ወላይታ ድቻ ሀዋሳን ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያጫወተው ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ ይህን ጨዋታ ለመምራት ተመድቧል። አርቢትሩ በጥቅሉ በዘጠኝ ጨዋታዎች 35 የቢጫ ካርዶችን ሲመዝ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱሉይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ

ብሩክ ቃልቦሬ – ኢስማኤል ሳንጋሪ

ኤፍሬም ዘካርያስ – አዲስ ህንፃ – በረከት ደስታ

ከነዓን ማርክነህ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ወንድማገኝ ማዕረግ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – አክሊሉ ተፈራ – ሄኖክ ድልቢ– ታፈሰ ሰለሞን – ደስታ ዮሀንስ

አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡