ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደደቢት ከ ድሬዳዋ ከተማ

ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚደረገው ብርቱ ፉክክር የብዙዎች ትኩረት የሳበው የሁለቱም ቡድኖች ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬን ከቀጠሩ በኃላ በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኙት ሰማያዊዎቹ ባለፉት የሜዳቸው ጨዋታዎች ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ሲታዩ በነገው ጨዋታም ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆኑ ይጠበቃል። ባለፉት ጨዋታዎች መድሃኔ ብርሃኔ እና ዳግማዊ አባይ በተሰለፉበት ያጋደለ የማጥቃት አጨዋወት ሲከተሉ የቆዩት ደደቢቶች ከዚህ አቀራረብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የማጥቃት አጨዋወትን እንደሚከተሉ ሲገመት ጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘው መድሃኔ ብርሃኔን በአምስት ቢጫ ማጣታቸውን ተከትሎ አዲስ የፊት የመስመር ጥምረት እንደሚያስመለክቱን ይጠበቃል። ከማጥቃቱም ባለፈ ጥሩ የመከላከል ባህርይ ባላቸው የመስመር አማካዮች የተዋቀረው የደደቢት አማካይ ክፍል በነገው ጨዋታ ፈጣኑን የድሬዳዋ የመስመር አጨዋወት መመከት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዕቅድም እንደሚኖራቸው ይገመታል።

ከዚህ በተጨማሪ ከማጥቃት አጨዋወቱም ባለፈ ከመቼውም የዓመቱ ወቅት በላይ የጠንካራ ተከላካይ ክፍል ባለቤት የሆኑት ደደቢቶች በኢታሙንዋ ኩሜይኒ የሚመራውን የድሬዳዋ የማጥቃት ክፍል ለመከላከል እንደባለፈው የሜዳቸው ጨዋታ ወደ መሀል ሜዳ የቀረበ አቋቋም ይዘው ሊቀርቡም ይችላሉ። ሰማያዊዎቹ ባለፈው ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ወሳኝ አጥቂያቸው ፉሴይኒ ኑሁ እና አጣማሪው መድሃኔ ብርሃኔን በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ሲያጡ ኩማ ደምሴ እና ሙሴ ዮሃንስም በጉዳት ቡድናቸውን የማያገለግሉ ተጫዋቾች ናቸው።

በሜዳቸው ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፉ በኋላ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ጥለው የደረጃ መንሸራተት አሳይተው የነበረቱት ብርቱካናሞዎቹ ባለፈው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርን አሸንፈው ከወራጅ ቀጠናው በአስተማማኝ ሁኔታ ለማምለጥ የጀመሩትን ጉዞ በነገው ጨዋታም ማስቀጠል የግድ ይላቸዋል።

ነገ ከሌሎች የሜዳ ውጪ ጨዋታዎቻቸው በአንፃራዊነት የተሻለ ቀለል ያለ ጨዋታ የሚጠብቃቸው ድሬዎች በተሻለ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ይጠበቃል። በውድድሩ አጋማሽ ልምድ ያላቸው አማካይ ተጫዋቾችን አስፈርመው መሀል ክፍላቸው ያጠናከሩት ድሬዎች በነገው ጨዋታ ከመስመር በሚነሱ ጥቃቶች የሰማያዊዎቹን ተከላካይ ክፍል ይፈትናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመስመር አጨዋወት ይበልጥ ውጤታማ እየሆኑ ያሉት ድራዎች በባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ጎሎች በተጠቀሰው የተሻጋሪ ኳስ መነሻነት በጭንቅላት ተገጭተው አስቆጥረዋል። ድሬዎች ፍቃዱ ደነቀን በጉዳት በረከት ሳሙኤልን ደግሞ በቅጣት የማያሰልፉ ሲሆን ራምኬል ሎክ ከጉልበት አንተነህ ተስፋዬ ደግሞ ከታፋ ጉዳታቸው አገግመው ለጨዋታው የሚደርሱ ይሆናል።

እርሰ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ እስካሁን በሊጉ 13 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን 3 ጊዜ አቻ ሲለያዩ ደደቢት ሰባት ጊዜ ድሬደዋ ደግሞ ሦስት ጊዜ አሸንፈዋል። ከተቆጠሩት 23 ግቦችም ደደቢት የ16ቱ ድሬዳዋ ደግሞ የዘጠኙ ባለቤቶች ናቸው።

– በትግራይ ስታድየም እስካሁን አስር ጨዋታዎችን ያደረገው ደደቢት ሁለት ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ሲያስመዘግብ በሌሎቹ ተሸንፏል።

– ከዘጠኝ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች አንዴ ብቻ ድል የቀናቸው ድሬዳዋ ከተማዎች አምስት ጊዜ ደግሞ አንድ ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል።

ዳኛ

– ጨዋታውን ለመምራት የተመደበው ብርሀኑ መኩሪያ እስካሁን በዳኘባቸው አምስት ጨዋታዎች 14 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት እና አንድ የሁለተኛ ቢጫ ካርድ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደደቢት( 4-2-3-1)

ረሺድ ማታውኪል

ዳግማዊ ዓባይ – አንቶንዮ አቡዋላ – ኃይሉ ገብረእየሱስ – ሄኖክ መርሹ

የዓብስራ ተስፋዬ – ኤፍሬም ጌታቸው

ሙሉጌታ ዓምዶም – አለምአንተ ካሳ – እንዳለ ከበደ

ቢኒያም ደበሳይ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ዘነበ ከበደ – ሳሙኤል ተስፋዬ

ረመዳን ናስር – ሚኪያስ ግርማ – ኤልያስ ማሞ – ምንያህል ተሾመ

ሐብታሙ ወልዴ – ኢታሙና ኬይሙኒ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡