ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ስሑል ሽረ

ነገ ከሚደረጉት ሰባት ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የጅማ አባ ጅፋር እና ስሑል ሽረ ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።

በሁለተኛው ዙር ከመሪዎቹ የማይተናነስ ነጥብ በመሰብሰብ በሊጉ ወገብ የሚገኙት ጅማዎች ከመሪዎቹ ያላቸውን ነጥብ ለማጥበብ ወይም ጠብቆ ለማስቀጠል የነገውን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተው ነው የሚያከናውኑት። ተከታታይ ድሎች ከማስመዝገብ አልፈው መረባቸውንም ሳያስደፍሩ እስከ ባለፈው ጨዋታ ድረስ መጓዝ ችለው የነበሩት ቻምፒዮኖቹ ናይጀርያዊው የቀድሞ አጥቂያቸውን መልሰው ካገኙ በኃላ እንዳደረጓቸው ጨዋታዎች ነገም ግዙፉ አጥቂያቸው ኦኪኪ ኦፎላቢን መሰረት ያደረገ አጨዋወት ይጠቀማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ በዋነኝነት ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ ሰጥተው በሚጫወቱት አማካዮች የተሞላው ጅማ አማካይ ክፍሉ በአንፃራዊነት ከነሱ የተሻላ በመከላከል ባህሪ ባላቸው አማካዮች ከተሞላው ስሑል ሽረ የሚጠብቃቸው ፈተና በጨዋታው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። በቡድኑ ስብስብ ውስጥም ከዐወት ገብረሚካኤል መሰለፍ አጠራጣሪነት ሌላ የተሰማ የጉዳት እና ቅጣት ዜና የለም።

በሁለተኛው ዙር አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን ቀጥረው ከመጀመርያው ዙር በተሻለ ጥሩ መንፈስ ሊጉን ጀምረው ውጤታቸው በድል ማጀብ ያልቻሉት ስሑል ሽረዎች በሊጉ ለመቆየት በሚያደርጉት ትግል ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ወደ ጅማ በማቅናት ያደርጋሉ። ከሌሎች የቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው አንፃር በዚህ ሳምንት ጠንከር ያለ ጨዋታ የሚጠብቃቸው ሽረዎች መከላከል ላይ ያመዘነ አጨዋወትን ይመርጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ እንደባለፉት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ከመስመር ወደ ረጃጅሞቹ አጥቂዎች በሚሻገሩ ኳሶች ባለሜዳዎቹን የመፈተን ዕድሉ ይኖራቸዋል። ሆኖም ቡድኑ ባለፈው ከሜዳው ውጪ ባደረጋቻው ጨዋታዎች የታዩበትን ከፍተኛ የመከላከል ችግሮች ፈትቶ ካልገባ በሁለተኛው ዙር በጥሩ መነቃቃት ከሚገኙት የጅማ ፈጣኖቹ የመስመር አጥቂዎች የሚጠብቀው ፈተና ትልቅ መሆኑ ለመገመት አያዳግትም። በቤተሰብ ችግር ወደ ፈረንሳይ ያቀናው አጥቂውን ሳሊፉ ፎፎና ከፈረንሳይ መልስ ቡድኑን የሚገለግል ቀሪው የቡድኑ ስብስብ በሙሉ ጤንነት ይገኛል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ለጅማ የዓመቱ ሁለተኛ ጨዋታ በነበረው የአምስተኛው ሳምንት የቡድኖቹ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ግንኙነት ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።

– ጅማዎች በሜዳቸው ዘጠኝ ጨዋታዎችን ሲያደርጉ አንዴም ሽንፈት ሳያገኛቸው የቀጠሉ ሲሆን አራት ጊዜ ድል ሲያደርጉ አምስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ባለፉት አምስት የሜዳ ላይ ጨዋታቸውም መረባቸውን አላስደፈሩም።

– ስሑል ሽረ ከሜዳው ውጪ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ሲያደርግ በአንድ ድል እና በሁለት የአቻ ውጤቶች አምስት ነጥቦችን ሲያሳካ ስድስት ሽንፈቶች ገጥመውታል።

ዳኛ

– ጨዋታው ለኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ስድስተኛ ጨዋታው ይሆናል። እስካሀን 20 የምስተጠንቀቂያ ካርዶች እና አንድ የፍፁን ቅጣት ምት የሰጠው ለሚ ጅማ አባ ጅፋር አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመበተን ጨዋታ ሲዳኝ ስሑል ሽረን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኛል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ዳንኤል አጄዬ

ዐወት ገ/ሚካኤል – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ

ይሁን እንዳሻው – አክሊሉ ዋለልኝ – መስዑድ መሐመድ

ማማዱ ሲዲቤ – ኦኪኪ አፎላቢ – አስቻለው ግርማ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – አሳሪ አልመሐዲ – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ረመዳን ዮሴፍ

ሐብታሙ ሸዋለም – ደሳለኝ ደበሽ

ሳሊፍ ፎፎና – ያስር ሙገርዋ – ቢስማርክ ኦፖንግ

ቢስማርክ አፒያ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡