ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና

የዛሬው የመጨረሻ የቅድመ ዳሰሳ ትኩረታችን የጊዮርጊስ እና ሲዳማ ጨዋታ ይሆናል።

የሊጉን መሪዎች በተወሰነ ርቀት ከሚከተሉ ክለቦች ውስጥ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ነገ 10፡00 ላይ በ20ኛ ሳምንት የሊግ ጨዋታቸው እርስ በርስ በአዲስ አበባ ስታድየም ይገናኛሉ። አንድ ደረጃን የማሻሻል ተስፋ ያላቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች አሁንም ወቅታዊ አቋማቸውን ማስተካከል አልቻሉም። ከ13ኛው ሳምንት በኋላ አዳማ ከተማን ካሸነፉበት ጨዋታ ውጪ ድልን ማጣጣም ያልቻሉት ፈረሰኞቹ ግብ የማስቆጠር ችግራቸውም አብሯቸው የቀጠለ ሆኗል። በቡድኑ የጉዳት ዝርዝር ውስጥም ከመሀሪ መና ፣ ሳላዲን ሰዒድ ፣ ለዓለም ብርሀኑ እና ጌታነህ ከበደ በተጨማሪ ምንተስኖት አዳነም የተካተተ ሲሆን ሳላዲን በርጌቾ ደግሞ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት ምክንያት ጨዋታው ያልፈዋል። ጨዋታውን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የሚገቡት ጊዮርጊሶች ተጋጣሚያቸው መሀል ሜዳ ላይ በቀላሉ የበላይነትን የሚወስድ አይነት ባይሆንም እነሱም ከአጥቂ ጀርባ ባለው ቦታ ላይ ካለባቸው ድክመት አንፃር የመስመር ተመላላሾቻቸው የማጥቃት ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ የማጥቃት ዕቅድ እንደሚኖራቸው ይታሰባል።

አዳማ ከተማን ሜዳው ላይ አስተናግዶ ወደ ድል የተመለሰው ሲዳማ ቡና ከዚያ አስቀድሞ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካቱ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ በሚፈልገው ፍጥነት እንዳይጓዝ አድርጎታል። ከሜዳ ውጪ ያለውን ደካማ ውጤትም መቅረፍ ሳይችል ነው ለነገው ከባድ ጨዋታ የደረሰው። መሀል ላይ ከያዟቸው ተጫዋቾች የአጨዋወት ባህሪ አንፃር ኳስን ለረጅም ጊዜ ከመያዝ ይልቅ በፍጥነት ወደ መስመር አጥቂች በማሳለፍ በቶሎ ወደ ሳጥን ለመድረስ ጥረት የሚያደርጉት ሲዳማዎች የመከላከል ኃይላቸው ላይ ተጨማሪ ጥንቃቄ በማድረግ በተመሳሳይ አቀራረብ ወደ ነገው ጨዋታ እንደሚቀርቡ ይታሰባል። የጊዮርጊስ የመስመር ተመላላሾች የማጥቃት ተሳትፎ አንፃርም የሲዳማ መስመር አጥቂዎች በመስመር ይዘዋቸው ወደ ውስጥ በሚገቧቸው ኳሶች ከፈረሰኞቹ ሦስት የኋላ ተሰላፊዎች በግራ እና በቀኝ ከሚሰለፉ ተጫዋቾች ጋር የሚገናኙባቸው የአንድ ለአንድ ፍጥጫዎች ተጠባቂ ናቸው። ሲዳማ ቡናዎች ወሳኝ አጥቂዎቹ አዲስ ግደይ እና መሀመድ ናስርን በጉዳት ምክንያት የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። በተጨማሪም ግርማ በቀለ ለሁለተኛ ጊዜ በአምስት ቢጫ ካርድ ከቡድኑ ጋር ያላመራ ሲሆን ሚሊዮን ሰለሞን ግን የሚመለስለት ይሆናል፡፡ አዲስ እና መሀመድ ካልገቡም የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት ኃላፊነት በሀብታሙ ገዛኸኝ ላይ የሚጣል ይመስላል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 19 ጊዜ በሊጉ ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 13 ድል በማስመዝገብ የበላይ ነው፡፡ 5 ጊዜ አቻ ሲለያዩ ሲዳማ ቡና በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ጊዮርጊስን ያሸነፈበትን የ 2-1 ውጤት ዘንድሮ አስመዝግቧል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 28 ጎሎች ሲያስቆጥር ሲዳማ ቡና 8 አስቆጥሯል፡፡

– የአዲስ አበባ ስታድየም ላይ ዘጠኝ ጨዋታዎች ያከናወነው ቅዱስ ጊዮርጊስ አምስቱን ሲያሸንፍ ሦስት የአቻ እና አንድ የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግቧል።

– ሲዳማ ቡና ከድቻ ጋር በገለልተኛ ሜዳ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ሳይጨምር ከሜዳው ውጪ ሰባት ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ድል የቀናው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በተረፈ ሦስቴ ነጥብ ሲጋራ ሦስት ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።

ዳኛ

– ጨዋታው ፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ከመከላከያ እና ወልዋሎ ጨዋታ ግርግር በኋላ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም የሚመለስበት ነው። አርቢትሩ ዘንድሮ አራት ጨዋታዎችን የመራ ሲሆን ዘጠኝ የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ አንዴ በሁለተኛ ቢጫ በሌላ ጊዜ ደግሞ በቀጥታ ቀይ ካርድ ሁለት ተጫዋቾችን ከሜዳ ሲያስወጣ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችንም ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ግሩም አሰፋ – ፈቱዲን ጀማል – ሰንደይ ሙቱኩ – ዳግም ንጉሴ

ወንድሜነህ ዓይናለም – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዳዊት ተፈራ

ሐብታሙ ገዛኸኝ – መሐመድ ናስር – አዲስ ግደይ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)

ፓትሪክ ማታሲ

አስቻለው ታመነ – ፍሬዘር ካሳ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ 

አብዱልከሪም መሐመድ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ – ኄኖክ አዱኛ

ታደለ መንገሻ

አቤል ያለው – ሪቻርድ አርተር


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡