ከፍተኛ ሊግ ለ | መድን እና ወልቂጤ ከተማ ሽንፈት አስተናገደዋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 14ኛ ሳምንት ምድብ ለ ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ሲደረጉ መሪው መድን እና ተከታዩ ወልቂጤ ተሸንፈዋል። የአዲስ አበባ ከተማ እና ነገሌ አርሲ ጨዋታ ደግሞ በዝናብ ምክንያት ተቋርጦ ወደ ነገ ዞሯል።

ኦሜድላ ሜዳ ላይ በ8:00 ግርጌ ላይ የሚገኘው የካ ክፍለ ከተማን የገጠመው ኢትዮጵያ መድን 2-1 ተሸንፏል። በዝናባማ አየር ታጅቦ በጀመረውና በሚካኤል ጣዕመ ጥሩ ዳኝነት በተመራው ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ የሁለቱም ጨዋታ ኳስን ይዞ ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ኢትዮጵያ መድን ብልጫ ያሳየበት ነበር። በ4ኛው ደቂቃ ያሲን ጀማል አክርሮ መትቶ የወጣበት፤ በውድድር ዓመቱ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው አብዱለጢፍ ሙራድ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ወደግብ ሞክሮ አግዳሚ ለትሞ ወደ ውጭ የወጣበት እንዲሁም ሚካኤል ለማ ከምስጋናው ወልደዮሐንስ ጋር ተቀባብሎ በማለፍ ከሳጥኑ ጫፍ አክርሮ በመምታት ወደ ግብ ሳይቀየር የቀሩት ሙከራዎች መድን ጥሩ አጀማመር ለማድረጉ ማሳያ ነበሩ።

ቀስ በቀስ በማንሰራራት ወደ ጨዋታው ቅኝት መግባት የቻሉት የካዎች በግማሽ የውድድር ዓመት ወደ ቡድኑን የተቃላቀለው ማትያስ ሹመቴ የግል ጥረት ወደ ግብ መቅረብ ችለዋል። በ22ኛው ደቂቃ ማትያስ ላይ ከርቀት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ጆርጅ ደስታ እንደምንም ብሎ ያወጣበት የመጀመርያው የየካ ሙከራ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ማትያስ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል። ከ10 ደቂቃዎች በኋላም በድጋሚ የካዎች በሄኖክ ከበደ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ አክለው ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል።

በቀሪዎቹ የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎች መድኖች ውጤቱን ለማጥበብ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በ37ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሰለሞን ወዴሳ ሳይጠቀምበት ሲቀር በ44ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልለጢፍ ሙራድ በተመሳሳይ የግብ እድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቶ ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲሁም የጠራ የግብ እድል በመፍጠር መድኖች ተሽለው ታይተዋል። በ46ኛው ደቂቃ ምስጋናው ወልደዮሐንስ፣ በ50ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ብርሃነ፣ በ55ኛው ደቂቃ አብዱለጢፍ ሙራድ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገውም በግብ ጠባቂው ጥረት እና ኢላማቸውን ባለመጠበቃቸው ግብ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

መድኖች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጫና መፍጠራቸውን ቢቀጥሉም የካዎች የሁለት ግብ ልዩነቱን አሳልፈው ላለመስጠት እጅጉን ወደ ኋላ አፈግፍገው በመጫወታቸው ክፍተት ማግኘት ተስኗቸው ታይተዋል። በ84ኛው ደቂቃ ላይ አብዱለጢፍ ሙራድ ከቅጣት ምት ያስቆጠረው ጎልም ልዩነቱን ከማጥበብ የዘለለ ትርጉም ሳይኖራት ጨዋታው በየካ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዚሁ ምድብ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ እና ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ወላይታ ሶዶን ያገናኘው ጨዋታ ሶዶ ላይ ተከናውኖ በባለሜዳው 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ገና በሁለተኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወንድሙ ባስቆጠረው ግብ ሶዶዎች ለ64 ያህል ደቂቃዎች መምራት የቻሉ ሲሆን አህመድ ሁሴን ለወልቂጤ ግብ አስቆጥሮ አቻ ቢያደርግም ብዙም ሳይቆይ ጥላሁን በቶ ለወላይታ ሶዶ ሁለተኛውና የማሸነፍያውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ኦሜድላ ሜዳ ላይ 10:00 ሰዓት የጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ እና ነገሌ አርሲ ጨዋታ ለሰባት ደቂቃዋች ያህል እንደተከናወነ በጣለው ዝናብ ምክንያት ወደ ነገ 4:00 የተሸጋገረ ሲሆን አዲስ አበባ ስታዲየም እንዲከናወን ተወስኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡