ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ የሊጉን መሪ አሸነፈ

የ20ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባህር ዳር ላይ መቐለ 70 እንደርታን ያስተናገደው ባህር ዳር ከተማ በሳላምላክ ተገኝ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል።

ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች ወደ ሀዋሳ አምርተው ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ወንድሜነህ ደረጄ (ቀይ ካርድ)፣ ማራኪ ወርቁ እና ግርማ ዲሳሳን በማሳረፍ አቤል ውዱ፣ ሳላምላክ ተገኝ እና ወሰኑ ዓሊን በማሰለፍ ጨዋታቸውን ጀምረዋል። ተጋባዦቹ መቐለ 70 እንደርታዎች ደግሞ በሜዳቸው ወላይታ ድቻን አስተናግደው አንድ ለምንም ከረቱበት ጨዋታ ያሬድ ብርሀኑን በማውሊ ኦሴይ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

አስገራሚ የደጋፊ ድባብ በነበረበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከዚህ ቀደም በስታዲየሙ ባልተለመደ መልኩ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ተዘምሮ ተጀምሯል።

ከአምስት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ወንዶች ፕሪምየር ሊግ ዳኝነት በተመለሰችው ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የተመራው ጨዋታው ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ሲያስመለክት በርካታ የግብ እድሎችም ተስተናግደውበታል። በሚታወቁበት 4-3-3 አስተላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት የጣናው ሞገዶቹ ኳስን ተቆጣጥረው ወደ መስመር በመውጣት ጥቃቶችን ለመሰንዘር ጥረት አድርገዋል። በተቃራኒው ተጋባዦቹ መቐለ 70 እንደርታዎች ደግሞ በ4-4-2 ዳይመንድ አስተላለፍ በመግባት ቀጥተኛ አጨዋወትን ተከትለዋል።

ገና በጅማሮ ሙከራዎችን ያስመለከተን ጨዋታው በ3ኛው ደቂቃ ወሰኑ ዓሊ ከመስመር አሻግሮት አሌክስ ተሰማ ባወጣው እንዲሁም በ4ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ወሰኑ ለፍቃዱ ወርቁ አቀብሎት ፍቃዱ ባልተጠቀመበት ሙከራ ግብ ለማስተናገድ ተቃርቦ ነበር። በመቐለዎች በኩል የመጀመሪያ ሙከራ የተሰነዘረው በ6ኛው ደቂቃ ሲሆን ማውሊ ኦሴይ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ሚካኤል ደስታ አሻምቶት ያሬድ ከበደ በግንባሩ በመሞከር ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። በፈጣን ሽግግሮች የቀጠለው የጨዋታው ጅማሮ በ8ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግል ጥረቱ ወደ ግብ ደርሶ በሞከረው ሙከራ ተማሙቆ ቀጥሏል።

በሁለት አጥቂዎች የገቡት መቐለዎች በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ መሃል ሜዳ ተጠግቶ ሲከላከል የነበረውን የባህር ዳር የተከላካይ መስመር ሲረብሹ ተስተውሏል። በ19ኛው ደቂቃም ፈጣኑ አጥቂ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከግራ መስመር የተጣለለትን ኳስ በመጠቀም ጥሩ ሙከራ ሞክሮ ሃሪስተን አድኖበታል። በአንፃሩ ተረጋግተው ኳስን በመቆጣጠር ለመጫወት ሲጥሩ የነበሩት ባህር ዳሮች በ21ኛው ደቂቃ ባገኙት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ይበልጥ ወደ ግብ ቀርበው ነበረ። ከአንድ ደቂቃ በኋላም ድጋሜ ግብ ለማስቆጠር በቀኝ መስመር በኩል ያመሩት ባለሜዳዎቹ ሳላምላክ ተገኝ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል።

ወደ መሃል አጥበው ሲጫወቱ የነበሩት የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ተጨዋቾች የሚያገኙዋቸውን ኳሶች ለማውሊ እና ለአማኑኤል በረጅሙ በመላክ የአቻነት ግብ ፈልገዋል። በዚህም በ28ኛው ደቂቃ አማኑኤል ከርቀት የተሻገረለትን ኳስ ለማውሊ አመቻችቶለት በተሰነዘረ ጥቃት እጅጉን ለግብ ቀርበው ነበረ። ከ5 ደቂቃዎች በኋላ ራሱ ላይ የተሰራበትን ጥፋት አማኑኤል ገ/ሚካኤል በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ መቶ ለጥቂት ወጥቶበታል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮቻቸው ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት የጣናው ሞገዶቹ በ34ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበረ። በዚህ ደቂቃ የመስመር አጥቂው ወሰኑ ዓሊ ከመቐሌ ተከላካዮች ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ ለፍቃዱ ወርቁ አቀብሎት ቢያድግልኝ ኤሊያስ ከኋላ በመምጣት ኳሱን ወደ ውጪ አውጥቶታል። የአቻነት ግብ መፈለጋቸው ያላቆሙት መቐሌዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ባገኙት የመዓዘን ምት ግብ ለማስቆጠር ሞክረው መክኖባቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በባለሜዳዎቹ መሪነት ተጠናቋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከእረፍት ሲገቡ በአካል ብቃት ኢንስትራክተርነት እና የውድድር ታዛቢነት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሲሰሩ ለነበሩት ነገር ግን በሳምንቱ አጋማሽ ህልፈታቸው ለተሰማው መብራቱ አዲስ የህሊና ፀሎት በማድረግ ጨዋታቸውን ጀምረዋል። ከእረፍት መልስ እጅጉን ተጠናክረው የገቡት መቐለዎች የመከላከል ባህሪ ያለውን የአማካኝ መስመር ተጨዋች በማስወጣት የአጥቂ ባህሪ ያለውን አማካኝ አስገብተው በተሻለ ለማጥቃት ሞክረዋል። ገና በጅማሮውም ማውሊ ለዮናስ ገረመው አመቻችቶ ባቀበለው ነገር ግን ዮናስ ባልተጠቀመበት ኳስ ጫና ማሳደር ጀምረዋል።

በአንፃራዊነት ከመጀመሪያው አጋማሽ ተዳክመው የተንቀሳቀሱት ባህር ዳሮች የመሃል ሜዳው ብልጫ በመቐለዎች በመወሰዱ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሞክረዋል። በ55ኛው ደቂቃ ኤሊያስ አህመድ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት የቡድኑ አምበል ደረጄ መንግስቱ አክርሮ መቶ የመቐለን የግብ መስመር ለሁለተኛ ጊዜ ለመድፈር ሞክሯል። በድጋሚ ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ኤሊያስ የመቐሌ የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተከትሎ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መቶ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥሯል። የመቐለ ተጨዋቾች ትተውት የሚወጡትን ቦታ በፈጣኖቹ አጥቂዎቻቸው መጠቀማቸውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች ቀይረው ወደ ሜዳ ባስገቡት ግርማ ዲሳሳ ሙከራ እጅጉን ወደ ግብ ቀርበው ግብ ጠባቂው ፍሊፕ ኦቮኖ አምክኖባቸዋል።

ከእነዚህ ሶስት ሙከራዎች በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደ ራሳቸው ሜዳ አፈግፍገው የተጫወቱት የአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ተጨዋቾች ያገኙትን ሶስት ነጥብ አሳልፎ ላለመስጠት ተከላክለው ተጫውተዋል። በተቃራኒው ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ መቐለዎች በሙሉ ኃይላቸው ጥቃቶችን ከየአቅጣጫው ሰንዝረዋል። በ73ኛው ደቂቃ ማውሊ ከቀኝ መስመር የተጣለለትን ኳስ በመጠቀም ወደ ግብ የሞከረው ሙከራ ሐሪስተን ሄሱ ተቆጣጥሮታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ለባለሜዳዎቹ ግብ ያስቆጠረው ሳላምላክ ተገኝ በመቐለዎች ግብ ክልል የተሳሳተውን ኳስ ያገኙት መቐሌዎች ኳሱን ለያሬድ ከበደ በመስጠት አስደንጋጭ ሙከራ ሰንዝረው ወቶባቸዋል።

አሁንም የአቻነት ግብ መፈለጋቸውን የቀጠሉት መቐሌዎች በ83ኛው ደቂቃ ማውሊ ከጥሩ ቦታ ባገኘው የቅጣት ምት ሌላ አስደንጋጭ ሙከራ አድርገው ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። ሙሉ 90 ደቂቃዉ ተጠናቆ በጭማሪው ሰዓት የመዓዘን ምት ያገኙት መቐሌዎች ሶስተኛ ጥሩ ኳስ በጋብሬል አህመድ አማካኝነት ሞክረው ሀሪስተን አድኖባቸዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናግድ በባለሜዳው ባህር ዳር ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡