ሪፖርት | ፋሲል ከነማ በሜዳው ከደቡብ ፖሊስ ጋር ነጥብ ተጋርቷል

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች መካከል በዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም የተደረገው የፋሲል ከነማ እና ደቡብ ፓሊስ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል።

ከሳምንት በፊት ፋሲል በሜዳው መቐለን ባስተናገደበት ጨዋታ ከነበረው ማራኪ የደጋፊ ድባብ እና የተመልካች ቁጥር ቀንሶ በተካሄደው ጨዋታ ፋሲል ከነማ ከመሪው ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የሚረዳውን 3 ነጥብ ሳያሳካ ሲቀር በተቃራኒው ደቡብ ፓሊሶች አንድ ነጥብ ከባለሜዳው ጋር በመጋራት ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት ነጥቡን ከፍ ማድረግ ችሏል። ፋሲል ከነማዎች አዲስ አበባ ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ከተጋራው ቡድን ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ ሶስት ተጫዋቾችን በመለወጥ ሳማኬን በጀማል፣ ሰለሞን ሀብቴን በበዛብህ መለዮ እና ዓለምብርሃንን በሰዒድ ሀሰን በመቀየር ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተመሳሳይ እግዳዎቹ ደቡብ ፖሊሶችም በሜዳቸው በወልዋሎ 1–0 ከተሸነፈው ቡድናቸው ሶስት ተጫዎቾችን በመለወጥ አዳሙ መሐመድን በዘሪሁን አንሼቦ፣ ኪዳኔ አሰፋን በብሩክ አየለ፣ በረከት ይስሀቅን በብሩክ ኤልያስ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል ።

በመጀመሪያው አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች በሙከራ ደረጃ የተሻለ ቢሆኑም ኳሱን ተረጋግቶ መቆጣጠር ክፍተታቸው ነበር። ገና በ3ኛው ደቂቃ ወደ ደቡብ ፖሊስ የጎል ክፍል መድረስ የቻሉት ዐፄዎቹ በሱራፌል ዳኛቸው አማካኝነት ከሳጥን ውጭ አክርሮ ወደ ግብ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ሐብቴ አምክኖታል። 7ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ሙጂብ እና ዓለምብርሃን ሳጥን ውስጥ አንድ ሁለት የቀባብለው ሙጂብ ወደ ግብ የመታት ኳስ በግቡ አናት ላይ የወጣችበት ኳስ፣ 9ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ከአምሳሉ ጥላሁን የተሻገረለትን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የመከነበት እንዲሁም በ17ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው የደቡብ ፖሊስ አማካዮችን አታሎ ያሳለፈለትን ኳስ ሽመክት በጠንካራ ምት ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያስቀረበት ዐፄዎቹ በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች የፈጠሯቸው የግብ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ፋሲሎች ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጋቸውን በመቀጠል 26ኛው፣ 31ኛው፣ 36ኛው፣ 41ኛው እና 44ኛ ደቂቃዎች ላይ ቢሞክሩም የግብ ጠባቂው ሲሳይ ሆነዋል። በተቃራኒው ደቡብ ፖሊሶች በመጀመርያው አጋማሽ አንድ ጊዜ ብቻ ወደ ዐፄዎቹ የግብ ክልል የደረሱ ሲሆን 27ኛው ደቂቃ ላይ በሄኖክ አየለ ሳጥን ውስጥ ከ ብሩክ ኤልያስ ጋር ተቀባብሎ ወደ ግብ የሞከራትን ኳስ ጀማል ጣሰው ያዳነባት ሙከራ ነበረች።

ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በፋሲል በኩል ተደጋጋሚ አስጨናቂ ሙከራዎችን ሲያደርግ የነበረው ሙጂብ ቃሲም በ60ኛው ደቂቃ የጨዋታውን የመጀመሪያ ግብ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሯል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ በመልሶ ማጥቃት የፋሲል የጎል ክልል ሲቀርቡ የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች በ66ኛው ደቂቃ የመሃል ተከላካዩን ያሬድ ባየህን ስህተት ተጠቅመው በሄኖክ አየለ አማካኝነት ጎል አስቆጥረዋል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ፋሲሎች ጫና በመፍጠር ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ለማግኘት ያለመ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው አንድ አቻ ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ፋሲል ከነማ በ34 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ሲቀመጥ ደቡብ ፖሊስ በ18 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡