የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 ሲዳማ ቡና

10፡00 ላይ የተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በባለሜዳዎቹ 2-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች በጨዋታው ዙሪያ ይህን ብለዋል።

” በ2-0 ሳይሆን በ5-0 ውጤት መጠናቀቅ የነበረበት ጨዋታ ነው ” ስትዋርት ሀል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

” በ2-0 ሳይሆን በ5-0 ውጤት መጠናቀቅ የነበረበት ጨዋታ ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ አቤል ሀት-ትሪክ መስራት የሚችልበት ዕድል አምልጦታል። ብዙ ዕድሎች አምክነናል ፤ ጥሩ የቆሙ ኳሶች አጋጣሚዎችም ነበሩን ፤ ጫና ውስጥ ከተናቸው ነበር። በሁለተኛውም አጋማሽ በጥሩ ሁኔታ ብንጀምርም በተመሳሳይ ብዙ ኳሶች አምክነናል። በሊጉ ጥሩ ልምድ ያላቸው ሁለት አጥቂዎቻችን ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ናቸው። ከሁሉም ተጫዋቾች ግቦችን ማግኘት አለብን። አሁን ላይ ግን ትልቅ ችግራችን ነው። የግድ አስቆጥሩ ማለት አትችልም ። ሰዎች እንጂ ሮቦቶች አይደሉም። ጠንክረው እንዲሰሩ እና ከጨዋታ ዕቅዱ ጋር እንዲጣጣሙ ማድረግ ብቻ ነው የሚቻለው። በአጨራረስ ላይ ብዙ እየሰራን ነው። የአጥቂዎቻችን በራስ መተማመን በጥቂቱ ቀንሷል ብዙ ኳስም ስተናል እንጂ በጥቅሉ ጥሩ ነበርን ጥሩ ኳስም ተጫውተናል።”

ጫና ውስጥ ስለመሆናቸው…

” ጫና ውስጥ አይደለውም። ሁለት እና ሦስት የእንቅጠርህ ጥያቄዎች አሉኝ። ጫና ውስጥ ነህ የሚባለው ለረጅም ጊዜ ስራ የምታጣ ከሆነ ነው። እኔ ያ ችግር የለብኝም። ከዚህ ለቅቄ ሰኞ ሌላ ስራ መጀመር እችላለው። ለደጋፊው ፣ ለአመራሮቹ እንዲሁም ለተጫዋቾቹ ስል ማሸነፍ እፈልጋለው። ይህ ጫና ከሆነ ጫና ውስጥ ነው ሊባል ይችላል። በስራው ዙሪያ ግን ምንም ጫና የለብኝም።”

“ቡድናችን ጥሩ ነው ግን በሰራናቸው ስህተቶች ግብ ተቆጥሮብን ተሸንፈናል” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

” ስንጀምርም ለመጫወት ሞክረናል። ግን የግብ ባቂያችን ጊዜ አጠባበቅ ችግር እና ከተከላካዮች ጋር በነበረው አለመግባባት የመጀመሪያው ግብ ተቆጥሮብናል። ከዕረፍት መልስ ተጫዋቼች ቀያይረን ለመቆጣጠር ሞክረን ነበር። ሁለተኛው ጎል እስኪገባብንም ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ነገር ግን አዲስ ወደ ፊት ይዞ የሄደው ኳስ ለጎሉ ቅርብ እሱ ስለነበር 100℅ ፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጠን ይገባ ነበር። ከዚያ በኋላ ተጫዋቾቻችን በመረበሻቸው በሰንደይ እና ግብ ጠባቂያችን አለመናበብ ሁለተኛ ግብ ተቆጥሮ ተሸንፈን ወጥተናል። ጨዋታው ጥሩ ነበር። እነሱ በረጅም ኳስ ለመጫወት ሞክረዋል ፤ ለነሱ ምቹ ነበር። ለኛ ሜዳውም ምቹ ስላልነበር ጭቃም ስለነበር ኳሱን ይዘን መጫወት ተቸግረን ነበር። ቡድናችን ጥሩ ነው ግን በሰራናቸው ስህተቶች ግብ ተቆጥሮብን ተሸንፈናል።”

ስለሰንደይ ሙቱኩ ቅያሪ

” ቅያሪው ትክክለኛ ነበር። ምክንያቱም እሱ ከገባ በኋላ ተከላካይ ክፍላችን ተረጋግቶ ለመጫወት ሞክሯል። መጨረሻ ላይ የሰራውም ስህተት ከግብ ጠባቂው ጋር ስላልተግባቡ ነው እንጂ እስከዛ ድረስ ጥሩ ነበር። ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው አጋማሽ ሲያጠቁ እንደነበረው ከዕረፍት መልስ አላደረጉም። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡