የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-2 ሀዋሳ ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት አዳማ ከተማ በሜዳው በ ሀዋሳ ከነማ 2-1 ተሸንፏል። ከጨዋታው በኋላም የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች እንደሚከተለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።

አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

እነሱ ተጭነው ነው የተጫወቱት፤ እኛ ደግሞ ምንም ክፍተት አልሰጠንም። ሀዋሳ ከተማ ከሜዳው ውጭ ካሸነፈ ብዙ ጊዜው ነው። የዛሬውን ጨዋታ ይበልጥ እንድንፈልገው ያደረገን አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ሙሉ ሶስት ነጥብ አልያዝንም ነበር። ከሜዳ ውጭ አዳማን የሚያክል ትልቅ ቡድን ማሸነፍ እና ነጥብ መያዝ ማለት ከባድ ነው። ወደ አምስት የሚጠጉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በጉዳት እና በቅጣት ሳንይዝ ነው የገባነው። በታዳጊዎች ተጫውቶ ማሸነፍ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው።

መከላከልን አልመረጥንም በመጀመሪያው 10 ደቂቃ ግብ በማግኝታችን እንደማንኛውም ቡድን ነው የተጫወትነው። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች እናገባለን፤ ከዛ ይገባብናል። ባህርዳር ላይም የተፈጠረ ይህ ነው። ያ ጥንቃቄ ስለነበር ነው ኋላ ላይ የበዛነው። አዳማ ከተማ የማጥቃት እንቅስቃሴው በጣም ከባድ ነው። ያንን ክፍተት ባንዘጋው ግብ ያስቆጥሩብን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የመረጥነው መልሶ ማጥቃት ነው። ይህም ደግሞ ያዋጣን ይመስለኛል።

አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

እንዳያችሁት የጥንቃቄ ጉድለት የቡድናችን መንፈስ ረብሾታል። ለመነሳት ጥረት አድርገናል። ኳሶችን የምትስት ከሆነ አጋጣሚውን ተቃራኒ ቡድን ይጠቀምብሀል። ያገቡት ግብም ተነሳሽነታቸውን ጨምሮታል።

በአጠቃላይ የሀዋሳ ቡድን በቴክኒክ ደረጃ የተሻለ ነበር። ውጤት ለማስጠበቅ ያደረጉት ነገር ተሳክቶላቸዋል። ሁለተኛውን ግብ ስትመለከቱት በራሳችን ስህተት ነው። የትኩረት ማጣት ችግር ነበረብን። ቡድናችን ላይ ያንን አስተካክለን ለቀጣይ ጨዋታ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንሞክራለን ።

ቡልቻ ሹራን በመጀመሪያ ተሰላፊነት አለመጠቀም

ቡልቻ ከብዙ ጊዜ ጉዳት በኋላ ነው የተመለሰው። እሱን በአንዴ መጠቀም ከባድ ውሳኔ ነው። በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ ነው ለውጥ አምጥቶ 18 ውስጥ መግባት የቻለው። እንዳያችሁትም ተስፋ ሰጭ ነው።

የአሰልጣኝ ለወጥ እና ውጤቱ

ቡድኑ በዚህ ደረጃ መቀመጥ አይገባውም ። በአሰልጣኝ ለውጥ ለተባለው እኔ እዚህ ቡድን ውስጥ ብዙ ጊዜ የቆየሁ ነኝ ። ከረጅም ጊዜ በኋላ አሁን ነው እድሉን ያገኝሁት እና ያው ውጤቱ ላይ ተፅዕኖ አሳረፈ ለሚለው ነገር አይመስለኝም። ዋናው ትልቁ ነገር እግርኳስ እንደምታየው ነው። በስህተት የተሞላ ነው ለዚህም ውጤት ታጣለህ ። ስለዚህ ለቀጣይ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገን ደጋፊውን እናስደስታለን ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡