ከፍተኛ ሊግ ሀ | የምድቡ መሪ ነጥብ ሲጥል ሦስት ጨዋታዎች ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግረዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 14ኛ ሳምንት ምድብ ሀ እሁድ በሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ ሰበታ ነጥብ ሲጥል አክሱም አሸንፏል። ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግረዋል።

ኦሜድላ ሜዳ ላይ ፌደራል ፖሊስን የገጠመው ሰበታ ከተማ ያለ ጎል አቻ ተለያይቷል። ከጨዋታው በፊት ዝናብ በመዝነቡ የሁለቱም ቡድኖች አምበሎች እና ቡድን መሪዎች ልዩነት ይዘው የቀረቡ ሲሆን ፌዴራሎች ጨዋታው መደረግ አለበት ሲሉ በተቀራኒው የምድቡ መሪ የሆነው ሰበታ ያለመጫወት ፍላጎት ቢሳይም ሜዳው ኳስ ማንጠር በማስቻሉ ለ15 ደቂቃዎች ዘግይቶ ተጀምሯል።

ሜዳው ጭቃማ በመሆኑ ምክንያት ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ይዞ ከመጫወት ይልቅ በረጅሙ በመለጋት እና የአየር ላይ ኳሶችን በመጠቀም ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው የግብ ሙከራዎች በብዛት እንዳይታዩ አድርጓል። በሰበታ በኩል በ24ኛው ደቂቃ ላይ ዐቢይ ቡልቲ ከርቀት አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ምኞት ሲሳይ ካወጣት ኳስ ውጭ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን ባለሜዳው ፌዴራል ፖሊስ በአብነት ደምሴ እና ሰይፈ ዛኪር ያደረጉት የግብ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

ኃይል የተቀላቀለበት ነንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ ተጫዋቾች ላይ ጥፋት ተሰራ በማለት የሁለቱም ቡድን አመራሮች ተገቢ ባልሆነ መንገድ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ነበር። በተለይ የሰበታው አሰልጣኝ ቅሬታውን የሚሳይበት መንገድ ተመልካች ሊያነሳሳ ነው በሚል የፌዴራል ፖሊስ ቡድን መሪ ከሰበታው ቡድን መሪ ጋር ለእሰጣ ገባ የተገባበዙበት ክስተት በመጀመርያው አጋማሽ የታየ ነበር። በዚህም ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሩ በፊት የፀጥታ ኃይል በመጨመርና ደጋፊውን ከቡድን አባላት በመለየት እንዲከናወን ተደርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ፌዴራል ፖሊሶች ኳሱን ተቋጣጥረው ለመጫወት ጥረት ያሳዩ ቢሆንም ሰበታ በግብ አጋጣሚ ያልታጀበ ብልጫኝ ቀስ በቀስ መውሰድ ችሏል። የጨዋታው ደቂቃ በገፋ ቁጥር ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት በመበራከቱ በያንዳንዱ ፊሽካ የዳኛ ከባብ ሲስተዋል ጨዋታው መጠንቀቂያ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ተጫዋች ማዕሩፍ መሐመድ ላይ ከደጋፊ በተወረወረ ድንጋይ ቅንድቡ ላይ ተመቶ በመውደቁ በጠብታ የህክምና ቡድን የህክምና እርዳታ ተደርጎለታል። ከክስተቱ በኋላ የሰበታን ደጋፊዎች ከሜዳው እንዳይወጡ በማድረግ ድንጋይ ወርዋሪውን ለይቶ ለማውጣት በሚደረግ ጥረት ከ3 ደቂቃዎች በላይ የተቋረጠው ጨዋታ ቀጥሎ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

የሁለቱም ቡድን አመራሮች ተገቢውን የእግር ኳስ ህግ ከመከተል ይልቅ ለፀብ የሚያነሳሱ ቃላትን በመሰንዘር እንዲሁም ተጫዋቾች እርስ በእርስ መጎናተል ታጅቦ የተጠናቀቀው ጨዋታ ፍፁም እግርኳሳዊ ያልነበረ እና የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ ትኩረት የሚሻ እንደነበር አመልክቶ አልፏል።

አክሱም ከተማ አክሱም ላይ አቃቂ ቃሊቲ አስተናግዶ 3-2 አሸንፏል። ሁለት ፈጣን ግቦች በተከታታይ በተቆጠሩበት ጨዋታ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ሙሉጌታ ረጋሳ እና ሙሉዓለም በየነ አክሱምን በጊዜ ቀዳሚ ማድረግ ሲችሉ ኤርምያስ ዘለቀ ተጨማሪ አንድ ግብ በማከል የግብ ልዩነቱን ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሏል። ከእረፍት መልስ ተሻሽለው የገቡት አቃቂ ቃሊቲዎች አብዱልቃድር ናስር በ75ኛው ደቂቃ እና ሮቤል ጥላሁን በ84ኛው ደቂቃ ግቦችን አስቆጥረው ጨዋታው 3-2 ተጠናቋል።

በዚሁ ምድብ ተጠባቂ የነበሩት የለገጣፎ ለገዳዲ ከ ደሴ ከተማ፣ ወሎ ኮምበልቻ ከ ገላን ከተማ እንዲሁም ወልዲያ ከ ቡራዩ ከተማ ጨዋታዎች በወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታዎች ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፈዋል።

ቅዳሜ በተደረገ የምድቡ ጨዋታ ኤሌክትሪክ ወደ ባህር ዳር ተጉዞ አውስኮድን 4-3 ማሸነፍ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡