ጂኦቫኒ ኤልበር ባየርን በኢትዮጵያ ሊከፍተው ስላሰበው አካዳሚ ይናገራል

የባየርን ሙኒክ አምባሳደር የሆነው ብራዚላዊው የቀድሞ አጥቂ ጂኦቫኒ ኤልበር በኢትዮጵያ ሊገነባ ከታሰበው አካዳሚ ጋር በተያያዘ እና ታዳጊዎችን ለመመለከት ከሌሎች ኃላፊዎች ጋር በመሆን እሁድ አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።

ዛሬ አመሻሽ ላይ የባየርሙኒክ የረጅም ዓመት ስፖንሰር የሆነው የስፖርት ትጥቆች አምራች አዲዳስ በአዲስ አበባ የሚገኘው የምርት አከፋፋይ ድርጅት በአካል በመገኘት ጉብኝት አድርጓል። በጉብኝቱ ወቅት የቡንዲስ ሊጋው ዋንጫ ለተመልካች ክፍት የሆነ ሲሆን የፎቶ መነሳት መርሐ ግብርም ተካሂዷል። በመጨረሻም ጂኦቫኒ ኤልበር ከጋዜጠኞች ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል።

ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ ግንዛቤ አለህ?

ስለ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች የነበረኝ እውቀት ውስን ነበር። ኢትዮጵያ ከመጣው ጀምሮ ግን ያየሁት ነገር ከጠበኩት በላይ ነው። በስታዲየም በመገኘት ብዙ ተመልካች እንደሚከታተል፣ ህብረተሰቡ ለእግርኳስ ትልቅ ፍቅር እንዳለው አስተውያለሁ። በየመንገዱ ብዙ ሰው ኳስ ሲጫወትም ተመልክቻለው። ስለ ባየር ሙኒክም አብዛኛው ሰው እንደሚያውቅ መረዳት ይቻላል።

ባየር ሙኒክ በኢትዮጵያ አካዳሚ ይከፍታል?

አዎ። የመጣነውም ያንን ለመከታተል እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋገር ነው። የኢትዮጵያ እግርኳስን በጣም ማገዝ እንፈልጋለን። እዚህ አካዳሚ ውስጥ ታዳጊዎችን በማካተት ስለ እግርኳስ ታክቲክ አጠቃላይ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ እንፈልጋለን። የመጣነው ሀሳቦችን ሰጥተን ለመመለስ ብቻ አይደለም። ከባየርሙኒክ የሚመጡ የአካዳሚ አሰልጣኞች ስልጠና ይሰጣሉ፣ ታዳጊዎቹም ወደ ጀርመን እየሄዱ የሚማሩበትን እድል ማመቻቸት እንፈልጋለን።

አካዳሚው መቼ ይከፈታል? ምን ያህል ታዳጊዎችን በውስጡ ያካትታል ?

ከሰፖርት ሚኒስቴሩ ጋር ጥሩ ግኑኝነት አለን። አሁን ላይ ሆነን መቼ ይቋቋማል? ምን ያህል ታዳጊ በውስጡ አቅፎ ይይዛል? መቼ ይጀምራል? የሚለውን አሁን መመለስ አንችልም። ግን እየተነጋገርን ነው። በተቻለ መጠን በፍጥነት ለመጀመር እንሞክራለን።

አካዳሚው ተከፍቶ የሚሰለጥኑት ታዳጊዎች ወደ ባየርን ሙኒክ ሄደው የመጫወት እድል ያገኛሉ?

አሁን ትኩረት የምናደርገው ታዳጊዎችን በእግርኳስ ክህሎት ማብቃት፣ ማጎልበት፣ ማዳበር ላይ እና እዚሁ በሀገራቸው የሚጫወቱበትን መንገድ ማመቻቸት ነው። በቀጣይ በባየር ሙኒክ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ የሚጫወቱበትን ዕድል ማመቻቸት እንፈልጋለን።

ባየር ሙኒክ አጠቃላይ የቡድኑ አባላት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት ዕድል ይኖር ይሆን ?

(እየሳቀ) ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ የማይሆንበት ምክንያት የለም። የባየር ሙኒክ ተጫዋቾችም እዚህ መምጣት ለኢትዮጵያውያን ተመልካች በጣም አስፈላጊ ነው። ባየር ሙኒክ አካዳሚ የሚጫወት በአባቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ የ14 ዓመት ታዳጊ ተጫዋች አለ። በጣም ተስፋ ያለው ታዳጊ ነው። ማን ያውቃል ይህ ልጅ ትልቅ ሆኖ ለባየርሙኒክ ዋናው ቡድን ሲጫወት የቡድኑ አባላትን ይዞ ሊመጣ ይችላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡