ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ስሑል ሽረ

ዛሬ በብቸኝነት በሃዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ የሚካሄደውን እና በሰንጠረዡ ሁለት ፅንፍ የሚገኙትን ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

የሊጉ መሪ ነጥብ በጣለባቸው ሳምንታት አሸንፈው ልዩነቱን የማጥበብ ዕድላቸውን ያመከኑት ሲዳማ ቡናዎች ከሌሎች የቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው አንፃር የተሻለ ቀለል ያለ ጨዋታ ሰለሚጠብቃቸው ይህን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ይላቸዋል።

ባለፉት ጨዋታዎች በሁለቱም መስመር በአዲስ ግደይ እና ሃብታሙ ገዛኸኝ ላይ የተመሰረተው የመስመር አጨዋወታቸው እንደተፈለገው ውጤተማ ያላደረጋቸው ሲዳማዎች በዚህ ጨዋታ ተገማች አቀራረባቸው ይቀይራሉ ተብሎ ሲጠበቅ የተለጠጠው የስሑል ሽረ ጠንካራው የማጥቃት አጨዋወት ለመግታትም የመስመር ተከላካዮቻቸው እንቅስቃሴ ከሌላው ግዜ በተሻለ ሚዛናዊ እንደሚያደጉ ይጠበቃል። የተሻለ ውህደት እና የቁጥር ብልጫ ካለው የአማካይ ክፍል ጋር ሲገናኝ በቀላሉ የበላይነት የሚወሰድበት የቡድኑ የመሀል ክፍልም ጨዋታው ሜዳው ላይ የሚከናወን መሆኑ እንዲሁም ግርማ በቀለን ከቅጣት መልስ ስለሚያገኝም ተሻሽሎ የመቅረብ ዕድል ይኖረዋል። ከዚህ ውጪ ሲዳማ ቡና በጉዳት የሚያጣው ብቸኛው ተጫዋች ግሩም አሰፋ ይሆናል።

ባለፉት ጨዋታዎቻቸው ጠንካራ ተፎካካሪ ከመሆን አልፈው ውጤት ማስመዝገብ ያልቻሉት ስሑል ሽረዎች በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ጥለው ከተፎካካሪዎቻቸው ላለመራቅ በዚህ ጨዋታ ነጥብ የማስመዝገብ ግዴታ ውስጥ ገብተው ነው ለጨዋታው የሚቀርቡት። ባለፉት ጨዋታዎች ነጥብ ጥለው ከወራጅ ቀጠና የሚወጡበት ዕድል ያባከኑት ሽረዎች ከጅማ አባ ጅፋር ጋር እንደተከተሉት መስመር ላይ ያተኮረ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ትኩረት አድርገው ይገባሉ ተብሎ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ በቤተሰብ ችግር ምክንያት ወደ ፈረንሳይ አቅንቶ ከጅማ ጨዋታ በፊት በመጨረሻው ሰዓት ወደ ቡድኑ የተቀላቀለው ወሳኙ አጥቂያቸው ሳሊፉ ፎፋና በሙሉ ጤና ከቡድኑ ጋር መኖሩ ለአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ትልቅ እፎይታ ነው። ስሑል ሽረዎች ከመስመር ተጫዋቻቸው ክፍሎም ገብረህይወት ውጪ ቀሪ ስብስባቸው በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛል።

የእርሰ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

– በሜዳቸው ሽንፈት ካልገጠማቸው ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሲዳማ ሀዋሳ ላይ አስር ጨዋታዎችን አድርጎ ሰባቱን በድል ሲወጣ በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎችም ነጥብ መጋራት ቿሏል።

– ስሑል ሽረ ከሜዳው ውጪ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ሲያደርግ በአንድ ድል እና በሁለት የአቻ ውጤቶች አምስት ነጥቦችን ሲያሳካ ስድስት ሽንፈቶች ገጥመውታል። 

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ሁለቱን ቡድኖች ለሦስተኛ ጊዜ የሚገኝበትን ጨዋታ ይመራል። ከዚህ ቀደም አርቢትሩ ሲዳማ ቡና ድቻ እና አዳማን እንዲሁም ስሑል ሽረ ሀዋሳ እና ፋሲልን በገጠሙባቸው ጨዋታዎች ላይ የተመደበ ሲሆን በጥቅሉም በዳኘባቸው አስር ጨዋታዎች በአማካይ 3.6 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ 2 የቀይ ካርድ እና 2 የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችንም አሳልፏል።
ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና ( 4-3-3)

መሳይ አያኖ

ዮናታን ፍሰሀ – ፈቱዲን ጀማል – ሰንደይ ምትኩ – ዳግም ንጉሴ

ወንድሜነህ አይናለም – ዮሴፍ ዮሃንስ – ግርማ በቀለ

ሀብታሙ ገዛኸኝ  –  መሓመድ ናስር – አዲስ ግደይ 

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሃፍቶም ቢሰጠኝ 

አብዱሰላም አማን – አሳሪ አልመሃዲ – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ረመዳን የሱፍ

ሃብታሙ ሽዋለም – ደሳለኝ ደባሽ 

ሳሊፉ ፎፋና – ያሳር ሙገርዋ – ቢስማርክ አፓንግ 

ቢስማርክ አፕያ

                            


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡