ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

በተመሳሳይ ጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኙትን ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ አሸንፈው በጥሩ መነቃቃት የሚገኙት ብርቱካናማዎቹ ይህ በሜዳቸው የሚያደርጉት ጨዋታ ከወራጅ ቀጠና ለመራቅ በሚደርጉት ጉዞ ወሳኝ እንደመሆኑ በዚህ ጨዋታ አጥቅተው ለመጫወት እንደሚገቡ ይታመናል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች መሃል ለመሃል ከሚያደርጉት ጥቃት ይልቅ በሁለቱም መስመሮች በመነሳት የሚሰነዝሩት ጥቃት ውጤታማ እያደረጋቸው የሚገኙት ብርቱካናማዎቹ በጨዋታው ያህንን አጨዋወት ይቀይራሉ ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም ተጋጣሚያቸው ወልዋሎ በሁለቱም መስመር የሚገኙትን ተጫዋቾች በማጥቃቱ ላይ እምብዛም የማያሳትፍ እና ለመስመር ጥቃቶች ልዩ ትኩረት አድርጎ የሚከላከል እንደመሆኑ አሰልጣኝ ስምዖን አባይ ውጤታማው አቀራረባቸውን ለዚህ አጨዋወት በሚመች መልኩ ይከልሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈም በዓመቱ መጀመሪያ ቀጥረዋቸው ከነበሩት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቡድን ጋር እንደመገናኘታቸው ተገማችነትን ፈፅመው ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል። ድሬዳዋ ከተማዎች እንዳለፉት ሳምንታት ሁሉ በነገውም ጨዋታ መሀል ተከላካያቸው በረከት ሳሙኤልን በቅጣት ሲያጡ ራምኬል ሎክ ደግሞ በጉዳት ሳቢያ ጨዋታው ያመልጠዋል ፤ ሆኖም ለረጅም ሳምንታት በጉዳት ቡድኑን ማገልገል ያልቻለው ፍቃዱ ደነቀ ደግሞ ወደ ሜዳ የሚመልስበት ጨዋታ ይሆናል።

እንደ ተጋጣምያቸው ሁሉ በተመሳሳይ በጥሩ የውጤት ጎዳና ላይ የሚገኙት እና የመጨረሻ የሜዳ ውጪ ጨዋታቸው አሸንፈው ከሜዳቸው ውጪ የነበራቸውን ክብረ ወሰን ያሻሻሉት ቢጫ ለባሾቹ በዚህ ጨዋታ ቀላል ግምት አይሰጣቸውም። ባለፉት ጨዋታዎች በፈጣሪ አማካይ እጦት የመስመር ተጫዋቾች በአስር ቁጥር ሚና ለማሰለፍ ተገደው የነበሩት ወልዋሎዎች በዚህ ጨዋታ አፈወርቅ ኃይሉን ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ለአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ትልቅ እፎይታ ነው። በአሰልጣኙ አጨዋወት ወደ ጎን በተለጠጡት የመስመር አማካዮች ቦታ አያያዝ እና ወደ ተከላካዮች በቀረበው የብርሃኑ አሻሞ እና አማኑኤል ጎበና ጥምረት ምክንያት በጎንዮሽ እና በቁመት ሰፊ ቦታ መሸፈን የሚጠይቀውን የአስር ቁጥር ሚና የሚፈልገውን ብቃት በተሻለ ያሟላው አፈወርቅ ኃይሉ ይረከበዋል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ባለፉት ጨዋታዎች በመስመር ላይ የተንጠለጠለው የቢጫ ለባሾቹ የማጥቃት አጨዋወት በዚህ ጨዋታ የተሻለ የፈጠራ አቅም ያገኛል ተብሎ ሲጠበቅ ባለፉት ጨዋታዎች ከተፈጥሯዊ ቦታው ውጪ አስር ቁጥር ሚና ላይ ለመሰለፍ የተገደደውና በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘው ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ወደ ተለመደ ቦታው ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል። ከዙህ ውጪ ቡድኑ የግራ መስመር ተከላካዩ ብርሃኑ ቦጋለን በህመም በረከት ገ/እግዚአብሄርን ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፍም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወልዋሎ ሊጉን በተቀላቀለበት የ2010 የውድድር ዓመት የተደረጉት ሁለቱም የእርስ በእርስ ጨዋታዎች በድሬዳዋ ከተማ 2-0 አሸናፊነት የተጠናቀቁ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ያለግብ ተለያይተዋል። ድሬዳዋ አምና ወልዋሎ ላይ ባሳካው የ30ኛ ሳምንት ድልም ነበር ዘንድሮ በሊጉ መቆየት የቻለው።

– ድሬዳዋ ከተማ ከተማ ሜዳው ላይ አስር ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን አራት የሽንፈት እና የድል ሁለት ደግሞ የአቻ ውጤት አስመዝግቧል።

– በስምንት አጋጣሚዎች ከትግራይ ስታድየም ውጪ የተጫወቱት ወልዋሎዎች ሦስት ጊዜ በሽንፈት ሲመለሱ ሁለት የአቻ እና ሦስት የድል ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል።

ዳኛ

– ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይመራዋል። አርቢትሩ በእስካሁኖቹ ዘጠኝ ጨዋታዎች 45 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲያሳይ አንድ ጊዜ በቀጥታ ቀይ ካርድ ሁለት ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተጫዋቾችን ለሜዳ አሰናብቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ዘነበ ከበደ – ያሬድ ዘውድነህ

ፍሬድ ሙሸንዲ – ሚክያስ ግርማ

ኤርሚያስ ኃይሉ – ምንያህል ተሾመ – ረመዳን ናስር

ኢታሙና ኬይሙኒ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

አብደልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን – ደስታ ደሙ – በረከት ተሰማ – ዳንኤል አድሀኖም

ብርሃኑ አሻሞ – አማኑኤል ጎበና

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – አፈወርቅ ኃይሉ – ኤፍሬም አሻሞ

ሬችሞንድ አዶንጎ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡