የአሰልጣኞች አስተያየት | ደደቢት 0-1 ጅማ አባ ጅፋር

ጅማ አባ ጅፋር ወደ መቐለ ተጉዞ ደደቢትን 1-0 ካሸነፈበት የ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞቹ የሰጡትን አስተያየት እነሆ

” ስንመጣ ጨዋታው የለም ተብለን ነበር፤ እንደውም ፎርፌ ነበር የተባልነው ” የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለ ጨዋታው

ኳስ ተቆጣጥሮ መጫወቱን ለነሱ ነው የፈቀድንላቸው። እኛ የተጫወትነው በ4-4-2 አሰላለፍ በመልሶ ማጥቃት ነው። ሆኖም ጨዋታውን ጨርሰን መውጣት የነበረብን ከዕረፍት በፊት ነበር። እነሱ ወደ ኳሱ ነው የተሳቡት እኛም ኳሱን ለነሱ ፈቀድንና ረጃጅም ኳስ ለማጥቃት ነበር የሄድነው። በዛ አጨዋወትም ግብ አግብተናል።

ስንመጣ ጨዋታው የለም ተብለን ነበር። እንደውም ፎርፌ ነበር የተባልነው፤ ያልጠበቅነውን ነው ያገኘነው።

ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት እነሱ የተሻሉ ነበሩ ለግብ ደሞ እኛ ቅርብ ነበርን ግብ በማስቆጠራችን አሸንፈን ወጥተናል።

ስለ ቡድናቸው

ቡድናችን ከጨዋታ ጨዋታ ለውጥ አለው። ከዚህ በፊት በ4-3-3 ነበር የምንጫወተው፤ አሁን 4-4-2 መርጠን ያለፉት ጨዋታዎች ውጤታማ ሆነናል። ሁለቱንም አጥቂዎች መሰረት አድርገን ነው እየተጫወትን ምንገኘው።

ጅማ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ አለ?

በርግጠኝነት። ከአሁን በኋላ ሲዳማ ቡናን ነው በሜዳችን የምንገጥመው። ሲዳማን ማሸነፍ ደሞ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ እንድንገባ ይረዳናል።

“ቁማር ሰርተው ነው እየመጡ ያሉት ” ይድነቃቸው ዓለሙ (የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ)

ስለ ጨዋታው

ወጣቶች በማደግ ላይ ያሉ ናቸው። ባለፉት ቀናት ስላልተከፈላቸው ደሞዝ ጥያቄ አቅርበው በዚ ቀን ይደርስላቸዋል ተብለው ስላልደረሰላቸው ልምምድ አቁመው ነበር። የቡድኑ አስተዳደርም አፋጣኝ እርምጃ ወስዶ በጥቂት ቀናት እንደሚከፈላቸው ቃል ገብቶላቸው በአንድ ቀን ልምምድ ነው ወደ ዛሬ ጨዋታ የገባነው። እንቅስቃሴያቸውም ከሞላ ጎደል ጥሩ ነበር።

የዛሬ ብቻ አደለም በኢትዮጵያ እግር ኳስ መታሰብ ያለበት። ቁማር ሰርተው ነው እየመጡ ያሉት ቡድኖች። ደደቢት ወራጅ ቀጠና ነው፤ ከደደቢት የግድ ሶስት ነጥብ ማግኘት አለብን። ይሄ ቡድን እንዲድን ይሄኛው ቡድን ነጥብ ማግኘት አለበት ተብሎ… አሁን እንዳያችሁት ብቻውን ሄዶ የኛ የነበረውን ኳስ ፊሽካ ነፍተው ቅጣት ሰጡ።
በጣም ብዙ ቦታ ያጫወተ ልምድ ያለው ዳኛ ነው። ከሱ የማይጠበቅ ስህተት ነው ሲሳሳት ያየነው። ይህ ነገር ቢታሰብበት። ክለቦች በዚ ዓይነት መንገድ የሚያመጡት ውጤት ጠቀሜታ የለውም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡