የግል አስተያየት | አሰልጣኝ ሥዩም እና 4-4-2 ዳይመንድ

አስተያየት በዘርዓይ ኢያሱ

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ባለፈው ዓመት ከሰበታ ከተማ ጋር የነበረውን ውል በስምምነት አቋርጦ መከላከያን ሲረከብ በወቅቱ ላለመውረድ ሲንገዳገድ የነበረውን ቡድን ከመውረድ በመታግ የቡድኑ ባለውለታ ሆኗል፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል ቡድኑን የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባለቤት በማድረግ በተጨዋቾቹና በክለቡ አመራሮች ዘንድ ከፍተኛ አመኔታን አግኝቷል፡፡ በመጀመሪያው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርኃ ግብር ከሜዳው ውጪ ደቡብ ፖሊስን 2ለ1 መርታት በመቻሉ መከላከያ በ2011 በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆን እንደሚችል ምልክት የሰጠ እና ለሻምፒዮንነት መጫወት የሚያስችል ብቃት እንዳለው በብዙሃን መገናኛዎች በሰፊው ተነገረ፡፡

ይሁን እንጂ በሒደት በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ለተጋጣሚዎቹ እጅ መስጠቱ በዚህ ፍጥነት ቡድኑ ለምን አሸቆለቆለ የሚል ጥያቄ አስከትሏል፡፡ ለአሰልጣኙ በአድናቆት ከጎኑ ቆመው የዘመሩሉትም ዛሬ በተቃራኒው ቆመው ትችቶችን ሲሰነዝሩ ታይተዋል፡፡

የአንድ ቡድን ውጤት ማጣት ቀጥታ ከስልጠና አልያም ከታክቲካዊ ጉዳዮች ጋር ከመያያዙ ባሻገር አስተዳደራዊ ጉዳዮችም የራሳቸው አሉታዊ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን የመከላከያ ወቅታዊ ችግር አስተዳደራዊ ሳይሆን ታክቲካዊ መሆኑን ከቡድኑ የሜዳ ውስጥ እንቅስቃሴ መገንዘብ ይቻላል፡፡ መከላከያ ሰፊ የቡድን ጥልቀት ካላቸው የፕሪምየር ሊጉ ጥቂት ቡድኖች መካከል አንዱ ቢሆንም ስብስቡና ከቅርብ ግዜ ወዲህ እያስመዘገበ ያለው ውጤት ሊጣጣም አለመቻሉን ተከትሎ ቡድኑ ላለመውረድ መጫወት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡

ማንኛውም አሰልጣኝ ከጨዋታ ምርጫ ጋር በተያያዘ የራሱ ምርጫ ይኖረዋል፡፡ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ከዚህ ቀደም እንደጠቀስኩት 4-4-2 ዳይመንድ የጨዋታ ፎርሜሽንን ከሚያዘወትሩ ጥቂት አሰልጣኞች መካከል አንዱ ነው፡፡
ነገር ግን የጨዋታ ምርጫው ውጤታማ ካላደረገው ስኬታማ የሚያርገውን አጨዋወት እስከሚያገኝ ድረስ የታክቲክ ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ የጨዋታ ፍልስፍና ልዩ እምነት ስላለው ቡድኑ ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን ቢያስተናግድም ሌሎች አማራጮችን ለማየት አልወደደም፡፡ አሰልጣኙ በአዲስ አበባ ስታድየም ባደረጋቸው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ከ4-4-2 ዳይመንድ ውጪ በአንዱ ብቻ ማሸነፉን ተከትሎ ታክቲካዊ ለውጥ ያደረገባቸው ጨዋታዎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡

በ4-4-2 ዳይመንድ አለማሸነፍ

ሥዩም በያዝነው የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ አበባ ስታድየም ያደረጋቸውን አስር ጨዋታዎች በ4-4-2 ዳይመንድ ፎርሜሽን ሲጀምር በሜዳው የመጀመሪውን ጨዋታ ያደረገው ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩንቨርሲቲ ጋር እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ ጨዋታ መከላከያ በሜዳው 1ለ0 ሲሸነፍ በወቅቱ የወልዋሎን መልሶ ማጥቃት መቋቋም ከብዶት እንደነበር ይታወቃል፡፡
በዚህ ጨዋታ መከላከያ በተጋጣሚው ብልጫ የተወሰደበት አሰልጣኝ ፀጋዩ ኪዳነ ማርያም በመሃለኛው የሜዳ ክፍል የቁጥር ብልጫ ስለወሰደበት ነው፡፡ ይህ ማለት በሥዩም የዳይመንድ ጨዋታ በአማካይ ስፍራ ተጨዋቾች መካከል ያለው ክፍተት ታክቲካዊ ይዘቱን ይዞ አለመቀጠሉና በቀኝና በግራ የሜዳ ክፍል ክፍት ቦታዎች መኖራቸው ነው፡፡ እነዚህን ክፍት ቦታዎች ደግሞ የወልዋሎ አዲግራት ተጨዋቾች በአግባቡ መጠቀም ችለዋል፡፡ አሰልጣኝ ሥዩም ውጤቱን ለመቀልበስ የተጨዋቾችም ሆነ የታክቲክ ለውጥ ቢያርግም በመከላከል ሽግግር በደንብ ተዋጥቶላቸው የነበሩትን የወልዋሎን ተጨዋቾች ማለፍ ተስኖት ስለነበር በሜዳ ሶስት ነጥብ ማግኘት አልቻለም፡፡

ወላይታ ድቻን በ4-3-3

ከወልዋሎው ሽንፈት በኋላ መከላከያ በሜዳው የገጠመው ወላይታ ድቻን ነበር፡፡ በዚህኛው ጨዋታ የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ መነሻ ፎርሜሽኑን እንደተለመደው 4-4-2 ዳይመንድ ሲያደርግ ጨዋታውን 3ለ1 አሸንፏል፡፡ ምንም እንኳን መከላከያ ጨዋታውን በድል ያጠናቀቀ ቢሆንም ሶስት ነጥቡ የተገኘው ግን በ4-4-2 ዳይመንድ አመለሆኑን ልናስተውል ይገባል፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የሥዩም መነሻ ፎርሜሽን 4-4-2 ዳይመንድ ነው፡፡ ቡድኑ በዚህ ፎርሜሽን በወላይታ ድቻ የጨዋታ ብልጫ ተወስዶበት እስከ መጀመሪያ ግማሽ 1ለ0 ሲመራ ቆይቶ ነበር፡፡ ከእረፍት መልስ አሰልጣኝ ሥዩም ያደረገው የተጨዋችና የፎርሜሽን ለውጥ በ2011 በአዲስ አበባ ስታድየም የመጀመሪያውን ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡

ሥዩም በዚህ ጨዋታ ሶስት ነጥብ የማግኘቱ ሚስጥር ብዬ የወሰደኩት ጨዋታውን ከ4-4-2 ዳይመንድ ወደ 4-3-3 መቀየሩ ነው፡፡ በዚህ ፎርሜሽን የአጥቂዎቹን ቁጥር ከሁለት ወደ ሶስት ከፍ ሲያደርግ ዳዊት ማሞና ፍቃዱ ዓለሙ ወጥተው ተመስገን ገ/ኪዳንና ፍፁም ገ/ማርያም መግባታቸው ለጎሎቹ መገኘት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች ከመግባታቸው በፊት ቡድኑ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶበት ነበር፡፡ ይህ ከሆነበት ምክንያት አንዱ የዳይመንድ ቅርፁ የመሃልኛውን የሜዳ ክፍል ስለሚያሳሰውና በግራና በቀኝ በኩል አማካዮች ወደ ውስጥ አጥብበው ሲጫወቱ ኮሪደሩ ክፍት ስለሚሆን ለተጋጣሚ ቡድን ምቹ በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ተመስገን ገ/ኪዳንና ፍፁም ገ/ማርያም ከገቡ ወዲህ የቡድኑ የማጥቃትም ሆነ የመከላከል ሚዛን ተስተካክሏል፡፡

የመከላከል ሚዛኑን መጠበቅ

ሁለቱ አጥቂዎች ሲገቡ የቡድኑ የማጥቃት ኃይል በመጨመሩ ተመስገን ገብረ ኪዳን ለሁለቱ ጎሎች መገኘት ምክንያት ሲሆን ፍፁም ገብረ ማሪያም ደግሞ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የመስመር አጥቂዎቹ ተቀይረው መግባታቸው የቡድኑን የመከላከል ሚዛን አስተካክሎታል፡፡ ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች በ4-3-3 የጨዋታ ፎርሜሽን ቡድኑ በሚከላከልበት ጊዜ ወደ ኋላ የመመለስ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ የዚህን ግዜ የመሃል ሜዳው በአምስት የመከላከያ ተጨዋቾች ስለሚያዝ በመስመርና በመሃልኛው የሜዳ ክፍል የነበረው ክፍተት ይዘጋል፡፡ ይህ ደግሞ እንደ መጀመሪያው ግማሽ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዳይወሰድበት አድርጓል፡፡ እንደውም ወላይታ ዲቻ አሳማኝ የጨዋታ ብልጫ ተወስዶበት ሶስት ነጥብ ለመከላከያ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ይህን ውጤት እንዲገኝ በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የተወሰደው ታክታካዊ ውሳኔ አስደናቂና ውጤቱም ይገባዋል ያስባለ ነበር፡፡ የሆኖ ሆኖ የሥዩም የጨዋታ መነሻው 4-4-2 ዳይመንድ መሆኑ ባያጠያይቅም ይህንን ጨዋታ ያሸነፈው በ4-3-3 መሆኑን ልናየው ያስፈልጋል፡፡ እናም ከዚህ የምንረዳው መከላከያ በሜዳው ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በ4-4-2 ዳይመንድ ለማሸነፍ መቸገሩን ነው፡፡

በ4-4-2 ዳይመንድ ብቸኛው ድል

ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በ15ኛው ሳምንት ያደረገው ጨዋታ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በ4-4-2 ዳይመንድ ያሸነፈበት ብቸኛ የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በቀሪዎቹ ዘጠኝ ጨዋታዎች በ4-4-2 ዳይመንድ ሶስት ነጥብ ማግኘት አልቻለም፡፡

ማጠቃለያ

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ከ20 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አራት ሲሆን በ4-4-2 ዳይመንድ በሜዳው ሲያሸንፍ ያየሁት ኢትዮጵያ ቡናን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አንደኛው አማራጭ የማያዋጣ ከሆነ ሌላኛውን አማራጭ መውሰድ ከአሰልጣኙ የሚጠበቅ ነበር፡፡ ሆኖም አሰልጣኙ ብቸኛውን አማራጭ መጠቀም በመምረጡ ቡድኑ ቁልቁል መውረዱን ቀጥሎ በመጨረሻም ከቡድኑ ጋር ተለያይተዋል፡፡


*በአስተያየት ዓምድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸኃፊውን እንጂ የድረ-ገጹን አቋም አይገልጹም፡፡

*ለጸኃፊው ያለዎትን አስተያየት በዚህ ኢሜይል አድራሻ መላክ ይችላሉ | zeray.eyassu@gmail.com