የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 5-0 ባህር ዳር ከተማ

ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም የተከናወነው የ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በቡና 5-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።

“ራሳችንን በደንብ የገለፅንበት ጨዋታ ነበር”
ገዛኸኝ ከተማ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለጨዋታው…

“ጥሩ ነገር ያየንበት እና ራሳችንን በደንብ የገለፅንበት ጨዋታ ነበር። ከዚህ በፊት የምንሰራውን ስራ ነው የሰራነው። ነገር ግን ውጤቱ ያስፈልገን ስለነበር ወደ አሸናፊነት ለመምጣት ተጫዋቾቹም ትልቅ መስዕዋትነት የከፈሉበት ትልቅ እና ድንቅ የሆነ ጨዋታ ነበር።”

ስለአቡበከር ቀይ ካርድ እና ተፅዕኖው…

“አቡበከር የወጣበት መንገድ እኔን አላሳመነኝም። ምክንያቱም የተማታው የነሱ ተጫዋች ነበር። ለምን ቀይ ካርድ እንደተሰጠውም አናውቅም ፤ በቀጣይ ትልቅ ተፅዕኖም ይፈጥራል።”

ስለአቡበከር ነፃ ሚና…

“ይህ ጉዳይ በመጀመሪያም በጨዋታ ዕቅዳችን ውስጥ ነበር። ነገር ግን ለመተግበር አጋጣሚዎቹ አልነበሩንም ፤ ተጫዋቾቻችን በጉዳት እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት መሉ ሳይሆኑልን ቀርተው ነበር። አሁን ግን የዛሬ ተጋጣሚያችንን ከዚህ ቀደም እናውቀውም ስለነበር ይህንን ብንጠቀም የተሻለ ነገር ያመጣልናል ብለን በማሰብ ተግብረነዋል።”

“በዛሬው ጨዋታ በሚገባ ተበልጠን ተሸንፈናል” ጳውሎስ ጌታቸው – ባህር ዳር ከተማ

ስለጨዋታው…

“ስለጨዋታው ከመናገሬ በፊት በጣም ብዙ ኪሎሜትሮችን አቋርጦ ለመጣው ደጋፊያችን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለው። በአጠቃላይ ተጫዋቾቼ ከመቐለው ጨዋታ በኋላ ራሳቸውን ትልቅ አድርገው ነበር። የመጀመሪያ ዕቅዳችን እንደዚህ አልነበረም። ያላሰብነው እና ያልጠበቅነው ጨዋታ ነበር። ይህም ውጤት ይገጥመናል ብለን አላሰብንም። አንድአንድ አጋጣሚዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። በአጠቃላይ በዛሬው ጨዋታ በትክክለኛው በሚገባ ተበልጠን ተሸንፈናል።”

የጨዋታውን አቅጣጫ የቀየሩ ክስተቶች…

” የመጀመሪያው ግብ ተጨርፎ ከተቆጠረብን በኋላ ለማጥቃት በምናስብበት ሰዓት የቡና የመልሶ ማጥቃት አመጣጣቸው እና ይኔ ተጫዋቾች ሰው አያያዛቸው በአጠቃላይ ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ድረስ ትክክል አልነበሩም። በጣም በጣም የተበላሸ ጨዋታ ነበር ፤ እንደዚህ ሆነን አናውቅም ከዚህ ቶሎ ለማገገም እንጥራለን። በአጠቃላይ ጨዋታው ስህተት ነበረው ተጋጣሚያችንም በልጦ አሸንፎናል። እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለው።”

የጨዋታ ዕቅድ…

“ባህር ዳር እንደምታውቁት አጥቅቶ የሚጫወት ቡድን ነው። ነገር ግን ዛሬ በመስመር የምንጫወተው ጨዋታ ተስብሮብናል። ኳስ ስናጋኝ መጫወት ብቻ ሆነ እና የእነሱ የመስመር ተከላካዮች ክፍተቶችን እንዲያገኙ ፈቀድንላቸው። ያንን ለማስተካከል ሞክረን ነበር። ብቻ በአጠቃላይ እኔም ተጫዋቾቼም ጥሩ ስላልነበርን ተበልጠን ተሸንፈናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡