ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ፋሲል ከነማ

የ21ኛው ሳምንት ማሳረጊያ እንደሚሆን የሚጠበቀው የጦሩ እና የዐፄዎቹን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ነገ አዲስ አበባ ላይ ዘግየት ብሎ በ10፡00 የሚጀምረው ጨዋታ በርካታ ግቦች በማስተናገድ ከፊት የተቀመጠው መከላከያ እምብዛም መረባቸውን ከማያስደፍሩ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ፋሲል ከነማን ያስተናግዳል። የድል ብርሀንን ካዩ ሰባት ሳምንታት ያለፏቸው መከላከያዎች ዳር ዳር ሲሉ ወደነበሩበት ወራጅ ቀጠና ገብተው እንዲሁም ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር ተለያይተው ነው ፋሲልን የሚገጥሙት። መከላከያዎች የሚቆጠሩባቸውን ግቦች መቀነስ ቢችሉም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በአንድ ጎል ልዩነት ለሽንፈት መዳረጋቸው አልቀረም። ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ ያሳኩት ፋሲሎችም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መልካም ነገር ቢታይባቸውም መሪውን በነጥብ ቀርበው ማስጨነቅ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች አምክነዋል። በሲዳማ የተነጠቁትን የሁለተኛነት ደረጃ ዳግም ለመረከብም ከመዲናዋ በድል መመለስ ይጠበቅባቸዋል።

በአሰልጣኝ በለጠ ገብረኪዳንን መሪነት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት መከላከያዎች ምን ዓይነት ለውጦችን አድርገው እንደሚመጡ ለመናገር ይከብዳል። ሆኖም በአሰልጣኝ ለውጦች ማግስት ቡድኖች የሚያሳዩት የመንፈስ ንቃት በጦሩም በኩል የሚጠበቅ ነው። ከዚህ ውጪ አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም ቡድኑን በያዙበት ወቅት ቀጥተኛነትን በተላበሰ መልኩ በቶሎ ወደ ጎል የሚደርስ ቡድን ይዘው እንደሚቀርቡ ሲገመት የተከላካይ ክፍሉን ተደጋጋሚ ስህተቶች እና በቀላሉ በተጋጣሚ የአማካይ ክፍል እየተዋጠ የመጨረሻ ኳሶችን ማድረስ የሚቸግረውን የመሀል ክፍሉን በቶሎ የማከም አጣዳፊ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። መከላከያ የፊት አጥቂው ምንይሉ ወንድሙን በጉዳት ተከላካዩ አበበ ጥላሁንን ደግሞ በቅጣት በነገው ጨዋታ መጠቀም አይችልም።

የአሰልጣኝ ውበቱ አባተው ፋሲል ከነማ አንድ የተከላካይ መስመር ተጨዋችን መስዋት በማድረግ ከኋላ በሦስት በሚጀምር አሰላለፍ የሚቀርብበትን አኳኋን በመቀየር የተወሰኑ የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በአጫጭር ቅብብሎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በመያዝ ለማጥቃት የሚሞክረው የቡድኑ የአማካይ ክፍል በተረጋጋ መንገድ ጫና መፍጠር መቻል ከነገ ተጋጣሚው ደካማ ጎን አንፃር ተጠቃሚ ሊያደርገው የሚችል ሲሆን የአጥቂው ሙጂብ ቃሲም ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ግብ ማስቆጠሩ መመለሱ ለጦሩ የኋላ ክፍል ተጨማሪ ስጋት መሆኑም አይቀርም። ለፋሲሎች በጨዋታው መጥፎው ዜና በሚመርጡት አጨዋወት ከኋላ ቅብብሎችን ለመጀመር ተመራጭ የሆነው ተከላከያቸው ያሬድ ባየህ ጉዳት ሲሆን የሱራፌል ዳኛቸው መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ለ6 ጊዜያት ተገናኝተው ዕኩል ሁለት ሁለት ጊዜ በመሸናነፍ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በጨዋታዎቹ ፋሲል ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር መከላከያ ስድስት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል፡፡

– አዲስ አበባ ላይ ዘጠኝ ጊዜ የክልል ቡድኖችን የገጠመው መከላከያ አንድ ጊዜ ብቻ ድል ሲቀናው ሦስቴ ነጥብ ተጋርቶ በአምስት ጨዋታዎች ተሸንፏል።

– ፋሲሎች ከጎንደር ወጥተው ባደረጓቸው አስር ጨዋታዎች ስድስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ ሁለት ጊዜ ድል አድርገው በሌሎች ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፈዋል።

ዳኛ

– መከላከያን ከጊዮርጊስ እንዲሁም ፋሲል ከነማን ከሀዋሳ ያጫወተው ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ይህን ጨዋታ ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን በዳኘባቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች አንድ የፍፁም ቅጣት ምት እና አንድ የቀጥታ ቀይ ካርድ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ 29 የማስጠንቀቂያ ካርዶችንም መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ – ምንተስኖት ከበደ – አዲሱ ተስፋዬ – ዓለምነህ ግርማ

ሳሙኤል ታዬ – ቴዎድሮስ ታፈሰ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ፍሬው ሰለሞን

ተመስገን ገብረኪዳን – ፍፁም ገብረማርያም

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሁሴን – ከድር ኩሊባሊ – ዓይናለም ኃይለ – አምሳሉ ጥላሁን

ኤፍሬን ዓለሙ – ሀብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡