ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መቐለ 70 እንደርታ ከ አዳማ ከተማ

በዚህ ሳምንት ከሚካሄዱት ጨዋታዎች አዝናኝ እንደሚሆን እና ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት የሚገመተውን ይህ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ተቀራራቢ አጨዋወት የሚከተሉት እና በአብዛኛው በፈጣሪ አማካዮች የተሞላ የመሀል ክፍል ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በነገው ጨዋታ አዝናኝ ጨዋታ ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከሁለተኛው ዙር መጀመር አንስቶ በወጣ ገባ ብቃት ውድድራቸውን እያካሄዱ የሚገኙት ምዓም አናብስት በነገው የሜዳቸው ጨዋታ ነጥብ መጣል አንገታቸው ስር መተንፈሰ ለጀመሩት ቡድኖች ጥሩ ተስፋ እንደመሆኑ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።

ባለፉት ጨዋታዎች በቅጣት እና በጉዳት ምክንያት በአስገዳጅ ሁኔታዎች ሳቢያ ጠንካራውን የያሬድ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል የፊት መስመር ጥምረት የቀየሩት አሰልጣኝ ገብረመድህን በነገው ጨዋታ ጥምረቱን የመመለስ ዕድላቸው የሰፋ እንደሆነ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ በ4-4-2 (የአማካይ ክፍሉ የጠበበ) በመስመር ማጥቃት ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸውን የመስመር ተከላካዮቻቸው በጉዳት አጥተው የነበሩት መቐለዎች የስዩም ተስፋዬ መመለስ መጠነኛ ፋታ ይሰጣቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ ባለፉት ጨዋታዎች ለተከላካይ ክፍሉ ጥሩ ሽፋን መስጠት ያልቻለው የአማካይ ክፍል ጥምረትም የተጫዋቾች ለውጥ ባይደረግበትም መጠነኛ የአጨዋወት ለውጥ ሊስተዋልበት እንደሚችል ይታመናል። ምዐም አናብስት አሁንም የአቼምፖንግ አሞስን ግልጋሎት የማያገኙ ሲሆን በአንፃሩ ግን ጉዳት ላይ የነበረው ስዩም ተስፋዬ ተመልሶላቸዋል።

ባለፈው ሳምንት በሃዋሳ ከተማ በሜዳቸው ያልተጠበቀ ሽንፈት የገጠማቸው አዳማ ከተማዎች በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ላለመጣል በዚፍ ጨዋታ አጥቅቶ መጫወት ብቸኛ አማራጫቸው ነው። ባለፉት ጨዋታዎች እንደተጋጣሚያቸው በአስገዳጅ ጉዳቶች አጨዋወታቸው ላይ በመጠኑም ቢሆን ለውጥ ለማድረግ የተገደዱት አዳማዎች ነገም እንደባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ለማጥቃት ይሞክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች በቡድኑ የሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ሚና ተሰጥቶት ሲጫወት የነበረው ከነዓን ማርክነህ በጉዳት ከቡድኑ ጋር አለመጓዙን ተከትሎ ቡድኑ አዲስ የማጥቃት ጥምረት ይሳያል ተብሎም ይገመታል።

ከፊት አጥቂያቸው ዳዋ ሆቴሳ መጎዳት በፊት በዋነኝነት በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ላይ ተመስርተው ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በሚገቡበት ወቅት የመስመር ጥቃትን ሲመርጡ የነበሩት አዳማዎች በዚህ ጨዋታ እንደ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የአማካይ ክፍል ባህሪ ያለው ተጫዋች በሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር የሚጠቀሙ ከሆነ መሀል ለመሀል የሚደረጉ ጥቃቶች ምርጫቸው ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይገመታል። አዳማዎች ሱሌይማን መሀመድን በ5 ቢጫ ካርድ ፤ ዳዋ ሆቴሳ ፣ ከነዓን ማርክነህ እና አንዳርጋቸው ይላቅ ደግሞ በጉዳት እንዲሁም ብዙአየሁ እንደሻውን በግል ጉዳይ ወደ መቐለ ይዘው አልተጓዙም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– መቐለ ሊጉን ከተቀላቀለበተ የ2010 የውድድር ዓመት ጀምሮ ከተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች አንዴ አንድ ጊዜ ሲሸነነፉ አንዴ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ አዳማ ሦስት መቐለ ደግሞ አራት ግቦች አስቆጥረዋል።

– ትግራይ ስታድየም ላይ 12 ጨዋታዎችን ያከናወነው መቐለ 70 እንደርታ አስር ጊዜ አሸንፎ ሁለቴ አቻ ተለያይቷል። ከጨዋታዎቹ በሰባቱ ግብ ሳያስተነግድ ከሜዳ መውጣት ችሏል።

– አዳማ ከተማ እስካሁን ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው አስር ጨዋታዎች መከላከያን በገጠመበት ጨዋታ ብቻ ነው ድል የቀናው። ከዛ ውጪ አራት ጊዜ ሲሸነፍ አምስቴ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ጨዋታውን ለመምራት ተመድቧል። በአምላክ በሊጉ አራተኛውን ጨዋታ የሚዳኝ ሲሆን በእስካሁኖቹ ሦስት ጨዋታዎች አራት የማስጠንቀቂያ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ

ፍሊፕ ኦቮኖ

ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚን ነስሩ – ሄኖክ ኢሳያስ

ያሬድ ብርሃኑ – ሚካኤል ደስታ – ጋብርኤል መሐመድ – ዮናስ ገረመው

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ያሬድ ከበደ

አዳማ ከተማ ( 4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱሌማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ተስፋየ በቀለ – ቴዎድሮስ በቀለ

ብሩክ ቃልቦሬ – ኢስኤል ሳንጋሪ

ኤፍሬም ዘካርያስ – አዲስ ህንፃ – በረከት ደስታ

ቡልቻ ሹራ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡