አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በድሬዳዋ ከተማ የሦስት ቀናት ቆይታ አደረጉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የድሬዳዋ እግርኳስን ለማነቃቃት፣ የታዳጊዎችን ስልጠና ለመቃኘት እና የተለያዩ የእግርኳሱ አመራሮችን ለማነጋገር አልመው ወደ ከተማዋ አምርተዋል።

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በድሬደዋ በነበራቸው ቆይታ የተለያዩ የተሳካ ተግባራቶችን ፈፅመዋል። በፕሪሚየር ሊጉ ድሬዳዋ ከ ወልዋሎ፣ በከፍተኛ ሊግ ድሬደዋ ፖሊስ ከ ኢኮስኮ ያደረጉትን ጨዋታዎች በስታዲየም በመገኘት መከታተል ከመቻላቸው ባሻገር የአሰልጣኝ መሠረት ማኒ ፕሮጀክት እና በአንድ ወጣት የሚመራ የታዳጊ ፕሮጀክት የስልጠና ሂደትን መመልከት ችለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የድሬዳዋ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድንን እንቅስቃሴን ተመልክተዋል። ከድሬዳዋ ስፖርት ኮሚሽን አመራሮች ጋር በቀጣይ በከተማዋ እግርኳስ እድገት ዙርያ ምክክሮችን ማድረጋቸውንም ለማወቅ ችለናል።

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በድሬደዋ ስለነበራቸው ቆይታ ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ብለዋል። ” የጉዞዬ ዋና አላማ አንድ የፕሪምየር ሊግ እና አንድ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎችን ለመከታተል ነው። ሊጉ ከተጀመረ ጀምሮ ለብሔራዊ ቡድን ምርጫ ሁሉንም እናዳርሳለን ብለን በገባነው ቃል መሠረት ከዚህ ቀደም ድሬዳዋ አልተገኘንም ነበርና ለመገኘት መጥቻለው። ከዚህ ውጭ የአካባቢውን ታዳጊዎች መጎብኘት ፣ ማበረታታት እና እነሱን የሚያሰለጥኑትን አሰልጣኞችን የሙያ ምክር ፣ ድጋፍ የመስጠትን ስራ አከናዉኛለው። ከድሬደዋ ስፖርት ኮሚሽነር ጋር በነበረኝ ቆይታ የክልሉን እግርኳስ ለማሳደግ ለአሰልጣኞች የሙያ ማሻሻያ እና የካፍ ላይሰንስ ፕሮግራም እንዲቀጥልላቸው ተናግረዋል። ይህን በተመለከተ ከፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በመነጋገር እንደምናግዛቸው ቃል ገብተናል። የእነርሱ ትልቁ ጥያቄ ይሄ ነው፤ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ምንም ዓይነት የማሻሻያ ሦልጠና ያላገኙ በመሆኑ እዚህ ላይ ትኩረት ሰተን እንድንሰራ ነግረውናል። ድሬዳዋን እንደምታቁት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ዕድገት ትልቁን ሚና ስትወጣ የቆየች ከተማ ናት። ብዙ እግርኳስ ተጫዋቾችን ማፍራት ችላለች። አቅሙ ስላለ እዚህ ላይ መስራት ነው የሚጠይቀው። አመራሮችም ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ነግረውኛል። እኛም በሚገባ የምናግዝ መሆናችንን ገልፀንላቸዋል። በመጨረሻ የተደረገልኝ መልካም አቀባበል በጣም ስሜት የሚነካ በመሆኑ በዚሁ አጋጣሚ በጣም ማመስገን እፈልጋለው።” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ አሰልጣኝ አብርሐም መብራቱ ብሔራዊ ቡድኖችን ለጨዋታ ከማዘጋጀት በተጓዳኝ ወደ ተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ የታዳጊዎችን ፕሮጀክት በመጎበኝት እና የአሰልጣኝ ስልጠናዎችን በመስጠት የተለያዩ ተግባራቶችን እያከናወኑ መሆኑ ይታወቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡