ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የአዳማ እና የቡና ጨዋታ የመጨረሻው የቅድመ ዳሰሳችን ትኩረት ነው።

ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግባቸው ከሚጠበቁ ጨዋታዎች ውስጥ የሚመደበው የአዳማ እና ቡና ጨዋታ ነገ 09፡00 ላይ በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታድየም ይከናወናል። ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ያገኙት አዳማ ከተማ ወደ ወራጅ ቀጠናው እየቀረበ ይገኛል። የመጀመሪያው ዙር ወጣ ገባ አቋሙን እንኳን ማስቀጠል ያልቻለው ክለቡ በሁለተኛው ዙር ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ስሑል ሽረን ሲረታ ብቻ ነበር ውሉ ነጥብ ማግኘት የቻለው። በመሆኑም ከበታቹ ያሉት ከለቦች ሳይጠጉት በፊት ነጥቡን ከፍ አድርጎ በሊጉ መደላደል ይጠበቅበታል። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ባህር ዳርን በሰፊ ጎል በመርታት ወደ ድል ተመልሷል። 32 ነጥብ ላይ የሚገኙት ቡናማዎቹ ጫና ውስጥ ባይገኙም ከአዳማ በአሸናፊነት መመለስ በመጠኑም ቢሆን ወደ ተንሸራተቱበት የዋንጫ ፉክክር ሊመልሳቸው ይችላል።

ሱለይማን ሰሚድ መቐለ ላይ በተመለከተው ቀይ ካርድ ዳዋ ሆቴሳ እና አንዳርጋቸው ይላቅ በጉዳት ብዙአየሁ እንደሻው ደግሞ ቅጣቱን ቢጨርስም ክለቡ የቅጣት ክፍያውን ባለመክፈሉ ለነገ የማይደርሱለት አዳማ መልካም ዜናዎችም አልጠፉትም። በዚህም በነገው ጨዋታ ሱለይማን መሀመድ ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት እንዲሁም ከነዓን ማርክነህ ከጉዳት ይመለሱለታል። በተለይም የከነዓን መመለስ ዳግም በሀሰተኛ አጥቂነት ሚና እንድናየው ሊያደርግ ባይችልም በታታሪ አማካዮች በተሞላው የተጋጣሚው የመሀል ክፍል ላይ በነፃነት የሚጫወት አማካይ ለሚያስፈልገው አዳማ መልካም ዜና ነው። እንደ ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ አምስት አማካዮችን ሊጠቀም የሚችለው አዳማ ለብቸኛው አጥቂው ቡልቻ ሹራ የሚሆኑ ኳሶችን ለማግኘት በከነዓን እና በጎኑ የሚኖሩት አማካዮች መካከል የተሳኩ ቅብብሎችን በመከወን በፈጣን ሽግግር በቡና አጋማሽ ለመገኘት እንደሚጥር ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሙሉ ግብ እየተቆጠረበት የሚገኘው የቡድኑ የኋላ ክፍል ለውጦች ሊደረጉበት እንደሚችሉ ይገመታል።

በባህር ዳሩ ጨዋታ ለአቡበከር ናስር ነፃ ሚናን በመሰጠት ባልተጠበቀ አቀራረብ ወደ ሜዳ ገብተው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የተዋጣለት 90 ደቂቃ ማሳለፍ ችለው ነበር። በፍጥነት ወደ ግብ የሚደርስ ፤ የተጋጣሚ ተከላካዮችን ፍጥነት በታከለባቸው ሰንጣቂ ኳሶች በማለፍ ከግብ ጠባቂው ፊት ሰፊ ክፍተት ሲያገኝ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥር በድንም መመልከት ችለናል። ሆኖም በዚህ ውስጥ ትልቅ ሚና የነበረው አቡበከር በቅጣት ነገ አለመኖር ለአሰልጣኝ ገዛኸኝ ትልቁ የቤት ስራ ነው። በዚህም የቡድኑን አሰላለፍ ሳይነኩ የአቡበከርን ሚና በተጫዋች መተካት ወይንም ከዛ በፊት ይጠቀሙበት ወደነበረው 4-3-3 መመለስ ከአሰልጣኙ ይጠበቃል። በእርግጥ ወደ መጀመሪያው ውሳኔ ሊያደሉ እንደሚችሉ የሚገመት ሲሆን ከሜዳ ውጪ የሚደረግ ጨዋታ እንደመሆኑ ግን ቡድኑ ሳምንት ያሳየንን ለመልሶ ማጥቃት የቀረበ አጨዋወት እንደሚተገብር ይጠበቃል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች 35 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 20 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ አዳማ ከተማ 6 ጊዜ አሸንፏል። በ9 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይለዋል።

– 94 ጎሎችን ባስተናገደው የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት ኢትዮጵያ ቡና 63፣ አዳማ ከተማ 31 ጎሎችን አስቆጥረዋል። በ2002 ቡና 6-1 ያሸነፈበት ውጤትም ከፍተኛው ነው።

– አዳማ ከተማ በሜዳው ካደረጋቸው አስር ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና ሦስት የአቻ ውጤትን ሲያስመዘግብ አምስት ጨዋታዎችን በድል መወጣት ችሏል።

– ስምንት ጊዜ ከአዲስ አበባ ስታድየም ውጪ ጨዋታዎቹን ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና ሁለት የድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶችን ሲያስመዘግብ አራት ጊዜ ተሸንፏል።

ዳኛ

– አዳማን ከአባ ጅፋር ቡናን ደግሞ ከሀዋሳ ያጫወተው ኃይለየሱስ ባዘዘው ይህን ጨዋታ የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ኃይለየሱስ በእስካሁኖቹ ሰባት ጨዋታዎች 15 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲያሳይ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችምን የሰጠ ሲሆን አንድ ጊዜ ደግሞ ሁለተኛ የቢጫ ካርድን መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ ( 4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱራፌል ዳንኤል – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ

አዲስ ህንፃ – ኢስኤል ሳንጋሪ

ኤፍሬም ዘካርያስ – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ቡልቻ ሹራ

ኢትዮጵያ ቡና (4-2-3-1)

ወንድወሰን አሸናፊ

አህመድ ረሺድ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ቶማስ ስምረቱ – ተካልኝ ደጀኔ

አማኑኤል ዮሀንስ – ሳምሶን ጥላሁን

እያሱ ታምሩ – ካሉሻ አልሀሰን – አስራት ቱንጆ

ሁሴን ሻቫኒ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡