ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መቐለ 70 እንደርታ

በዚህ ሳምንት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል የብዙዎችን ትኩረት የሳበው እና በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ወሳኝ የሆነ ጥቆማ ሊሰጥ የሚችለውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ከቅርብ ተቃናቃኞቻቸው አንፃር ሲታይ ደካማ ተከታታይ አቋም በማሳየት ለዋንጫ በሚደረገው ፉክክሩ ወጣ ገባ እያሉ ውድድራቸው እያካሄዱ የሚገኙት ፈረሰኞቹ ይህን የሳምንቱን ትልቅ ጨዋታ ማሸነፍ ይበልጥ ወደ ዋንጫ ፉክክር ስለሚያስጠጋቸው ከዚህ ፍልሚያ ሙሉ ሦስት ነጥቦችን የማሳካት ግዴታ ውስጥ ይገባሉ። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዚህ ዓመት በአመዛኙ 3-5-2 ምርጫቸው አድርገው ሲጫወቱ ቢቆዩም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙበት ወደነበረው 4-3-3 በመመለስ ነበር የቀረቡት። በነገው ጨዋታም በፈጣሪ አማካዮች የተሞላውን የመቐለ አማካይ ክፍል የቁጥር ብልጫ ለመውሰድ ወደቀደመው አደራደራቸው ለመመለስ ካልወሰኑ በስተቀር በ4-3-3 የሚገቡበት ዕድል የሰፋ እንደሆነ ይታመናል።

ከዚህ በተጨማሪ ይህን አሰላለፍ ምርጫቸው አድርገው በገቡባቸው ጨዋታዎች በሁለቱ የመስመር አጥቂዎች ላይ የተመሰረተ የማጥቃት አጨዋወት እና የፈጣሪ አማካይ እጥረት የተስተዋሉባቸው ፈረሰኞቹ በዚህ ጨዋታ በአማካይ ክፍል ላይ የቅርፅ ወይም የተጫዋቾች ለውጥ ካላሳዩ የመሃል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ እንደሚቸገሩ ይገመታል። ሳላሀዲን ሰዒድ፣ ጌታነህ ከበደ፣ መሀሪ መና እና ምንተስኖት አዳነ ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው የተጫዋቾቹን ግልጋሎት የማያገኙ ሲሆን በአንፃሩ አስቻለው ታመነ ከቅጣት አቤል ያለው ከጉዳት መልስ ቡድናቸው ለማገልገል ዝግጁ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው።

ሁለተኛው ዙር ከገባ በኋላ ከሜዳቸው ውጪ ነጥብ ይዘው ለመመለስ ሲቸገሩ የታዩት የሊጉ መሪዎች ምዓም አናብስት ከተከታዮቻቸው ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማስጠበቅ ወይም ለማስፋት ወደዚህ ጨዋታ ይቀርባሉ። ባለፉት ጨዋታዎች በማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸውን የመስመር ተከላካዮች በጉዳት ካጡ በኃላ በዛ ቦታ ሁነኛ ተተኪ አጥተው ሲቸገሩ እንደመታየታቸው ሥዩም ተስፋዬ፣ አንተነህ ገብረክርስቶስ እና ያሬድ ሐሰን በሙሉ ጤንነት መገኘታቸው ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው።

ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ በሚመቹ እና ከኳስ ውጪ በመንጠቅ ሂደት ላይ ብዙም አመርቂ እንቅስቃሴ በማያደርጉት ተጫዋቾች የተገነባው የመቐለ አማካይ ክፍል ባለፈው ጨዋታ በጉዳት ያልተሰለፈው ጋናዊው ጋብርኤል አሕመድ ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ከአዳማ ጋር በነበረው ጨዋታ ከጥልቅት እየተነሳ እንዲጫወቱ የተደረገው ሐይደር ሸረፋ ወደ ለአጥቂዎቹ ቀርቦ ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም ፈረስኞቹ ከሶስቱ አጥቂዎች በሁለቱም ጫፎች የሚገኙት ተጫዋቾች ላይ የተመሰረተ የማጥቃት አጨዋወት ስለሚከተሉ መቐለዎች ማጥቃቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው የመስመር ተከላካዮቻቸውን እንቅስቃሴ ሚዛናዊ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ምዓም አናብስት በዚህ ጨዋታ ከተከላካዩ አቼምፖንግ አሞስ ውጪ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በአንፃሩ ባለፈው ጨዋታ ቡድኑን ያላገለገለው ጋብርኤል አህመድ ወደ ሜዳ ይመለሳል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– እስካሁን በተገናኙባቸው ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ያልተሸነነፉት ሁለቱ ቡድኖች በዓምና ግንኙነተቸው ሁለት ጊዜ 1-1 ሲለያዩ የዘንድሮው ጨዋታቸው ደግሞ ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።

– የአዲስ አበባ ስታድየም ላይ አስር ጨዋታዎች ያከናወነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስድስቱን ሲያሸንፍ ሦስት የአቻ እና አንድ የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግቧል።

– መቐለ 70 እንደርታ ስምንት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን ሲያከናውን በመጀመሪያ ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ቢያገኘውም ቀጥሎ አቻ በመውጣት ከዚያም ሦስት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቧል ፤ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎቹ ደግሞ በፋሲል እና ባህር ዳር ተሸንፏል።

ዳኛ

– ዘጠኝ ጨዋታዎችን ዳኝቶ 41 የቢጫ ካርዶችን እንዲሁም አራት ቀጥታ ቀይ ካርዶችን የመዘዘው እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠው አሸብር ሰቦቃ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመይመራዋል። ሁለቱን ቡድኖች እስካሁን ያላጫወተው አርቢትሩ አራቱን ቀጥታ ቀይ ካርዶች የመዘዘው በመጨረሻ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በመራቸው ሁለት ጨዋታዎች ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

ሄኖክ አዱኛ – ሳላዲን በርጌቾ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ኢሱፍ ቡርሀና

ናትናኤል ዘለቀ – ሙሉዓለም መስፍን – ሀምፍሬይ ሚዬኖ

ሪቻርድ አርተር – አቤል ያለው – አቡበከር ሳኒ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፍሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ -አሚን ነስሩ -አንተነህ ገብረክርስቶስ

ያሬድ ከበደ – ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ – ሐይደር ሸረፋ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ኦሴይ ማውሊ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡