ሪፖርት | ዐፄዎቹ ከመሪው መቐለ የነበራቸውን ልዩነት ያጠበቡበትን ድል ድሬዳዋ ላይ አስመዝግበዋል


ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል በዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው ፋሲል ከነማ 2-0 በማሸነፍ ከመሪው ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት አጥብቧል።

ፋሲል ከነማዎች ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ መከላከያን አሸንፎ ከተመለሰው ቡድን ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ ዓለምብርሀን ይግዛውን በያሬድ ባዬ በመለወጥ ወደ ሜዳ ሲገቡ፤ እንግዳዎቹ ድሬድዋዎች በሜዳቸው ወልዋሎን 2-1 ካሸነፈው ቡድናቸው 3 ተጫዋቾች በመለወጥ ያሬድ ዘውድነህን በበረከት ሳሙኤል፣ ሳሙኤል ዮሐንስን በዘነበ ከበደ እንዲሁም ምንያህል ተሾመን በኤልያስ ማሞ ቀይረው ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በስፍራው ተገኝተው በተመለከቱት ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በማድረግ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን በጎሎች በማጀብ የበላይ መሆን ችለዋል። ገና በ6ኛው ደቂቃ ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል በመድረስ ሰለሞን ሐብቴ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፍሬው ሲያመክነው 8ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከመሐል ነጥቆ ለሙጂብ ቃሲም ያሻገረለትን ኳስ ሙጂብ በአስደናቂ አጨራረስ ወደ ጎል ቀይሮ ዐፄዎቹን ቀዳሚ አድርጓል።

ከጎሏ መቆጠር በኋላም ዐፄዎቹ በተደጋጋሚ አስጨናቂ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን 10ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ሀብቴ በግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ኢዙ አዙካ ግሩም ኳስ ቢሞክርም በጎሉ አናት ላይ ወጥታለች። ብዙም ሳይቆይ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ዓለሙ በአስደናቂ ሁኔታ 4ቱን የድሬዳዋ ተከላካዮች በማለፍ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል። ፋሲሎች ከጎሎቹ በተጨማሪ በተለይ በሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ሲችሉ እንግዳዎቹ ድሬደዋ ከተማዎች አልፎ አልፎ ወደ ፋሲል የጎል ክልል ቢደርሱም ፍሬያማ ሳይሆኑ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ የኳስ እንቅስቃሴ እና የሙከራ መቀዛቀዝ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ድሬዳዋዎች ተሻሽለው ቢቀርቡም ባለ ሜዳዎቹ በሙከራ የተሻሉ ነበሩ። 53ኛው ደቂቃ ላይ ሙጂብ ቃሲም ለሱራፌል ዳኛቸው ያቀበለውን ኳስ ሱራፌል ወደ ግብ አክርሮ መትቶ በግራ በኩል ስትወጣበት በ64ኛው እና 80ኛው ደቂቃ በሰለሞን ሀብቴ ተቀይሮ የገባው አብዱራህማን ሙባረክ ወደ ጎል ሳጥን ይዞ በመግባት የሞከራቸው ኳሶች ተጠቃሽ ነበረ። በድሬድዋዎች በኩል በ54ኛው ደቂቃ በፋሲል የጎል ክልል ውስጥ አንድ ሁለት ተቀባብለው ሞክረው ሚኬል ሳማኪ ያዳነው፤ 56ኛው እና 74ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በኤርምያስ ኃይሉ እና በምንያህል ይመር አማካኝነት ጠንከር ብለው የተመቱ ኳሶች ወደ ግብ ሳይቀየሩ ቀርተዋል።

ጨዋታው በፋሲል 2-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ዐፄዎቹ ነጥባቸውን 40 በማድረስ ከመሪው መቐለ ጋር የነበራቸውን ርቀት ወደ አምስት አጥብበው ለቻምፒዮንነት የሚያደርጉትን ፉክክር አጠናክረው ቀጥለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡