ስለ ዋልታ ፖሊስ ትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ የቡድኑ አሰልጣኝ ይናገራሉ

“ህዝቡ በቀጣይ ሶስት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ከዋልታ ፖሊስ ትግራይ ጎን እንዲቆም እንጠይቃለን” አሰልጣኝ ዮሐንስ ሲሳይ

ባለፈው ሳምንት ዓርብ መላው የእግርኳስ አፍቃሪ እጅግ ያሳዘነ ድርጊት በዋልታ ፖሊስ ትግራይ ላይ መፈፀሙ ይታወሳል። ከጥቃቱ በኃላም በስድስት የቡድኑ ተጫዋቾች ከባድ እና ቀለል ያለ ጉዳት ሲደርስ አማኑኤል ብርሃኑ የተባለ የቡድኑ ተጫዋችም ህይወቱን ማጣቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ቡድኑን ለበርካታ ዓመታት በአሰልጣኝነት የመሩት ዮሐንስ ሲሳይ (ምክትል ኢንስፔክተር) በቡድኑ፣ ጉዳት በደረሰባቸው አባላት ወቅታዊ የጤንነት ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ አጭር ቆይታ አድርገዋል።

የተጎዱት ተጫዋቾች ወቅታዊ የጤና ሁኔታ ምን ይመስላል?

ሁሉም የተጎዱ ህክምናቸው በአግባቡ እየተከታተሉ ነው ያሉት። እኔ ከዚህ ውጭ ጠለቅ ብዬ መናገር አልችልም። የህክምና ባለ ሞያዎች መልስ ካገኘን በኃላ ነው ለእንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች መልስ መስጠት የምንችለው።

ቡድኑ መቼ ወደ ልምምድ ይመለሳል?

በዚ ጉዳይ በቀጣይ ቀናት ከእግር ኳስ ፌደሬሽን እንነጋገራለን። ተጫዋቾች ስለተጎዱብን የህክምና ውጤታቸውን አይተን ከፌደሬሽኑ ጋር የምንነጋገር ነው የሚሆነው። በተጫዋቾቹ ላይ ከአካላዊ ጉዳት ባለፈ በስነ-ልቦና ላይም ጫና አለ። የቡድኑ ስነ-ልቦና ወደ ጥሩ ሁኔታ መመለስ ይኖርብናል። እሱን ከግምት አስገብተን ከፌደሬሽኑ ጋር ተነጋግረን ቡድኑን ወደ ልምምድ ለመመለስ ጥረት እናደርጋለን።

የተጎዱትን ተጫዋቾች እና የአማኑኤል ብርሃኑን ቤተሰብን ለመርዳት ጥረቶች ተጀምረዋል። ሂደቱ ምን ደረጃ ደረሰ?

ከክለቦች ጋር በፅህፈት ቤት ደረጃ ንግግር እያደረግን ነው። በዚ ሳምንት ሶስቱም ቀናት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አለ በምን መንገድ ድጋፍ መሰብሰብ እንደምንችል በንግግር ላይ ነው ያለነው። በትልቁ ግን ቤተሰቦችን እና ተጎጂዎች ላይ የሚደረገውን ነገር የትገረራይ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚቴ አዋቅሮ ሌላ ተመሳሳይ የድጋፍ ስራ የሚሰራ ነው የሚሆነው። በቀጣይ ጊዜያት በፖሊስ ኮሚሽን ስር የሚከናወኑ በርካታ የደጋፍ ስራዎች ይኖራሉ። ለጊዜው ግን በሚቀጥሉት ቀናት በሚደረጉት ሶስት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ከእግር ኳስ ቤተሰቡ ድጋፍ ለመሰብሰብ ነው እያሰብን ያለነው። ህዝባችንም ከዚ በፊት በርካታ ድጋፎች አድርጓል። አሁንም በነዚህ ጨዋታዎች ተመሳሳይ ድጋፍ በማድረግ ከዋልታ ፖሊስ ትግራይ ጎን እንዲቆም እንጠይቃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡