ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት የሀዋሳ እና ሲዳማ ጨዋታ ይሆናል።

በ22ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደው የተመለሱት ሀዋሳ እና ሲዳማ ነገ በጋራ ሜዳቸው ላይ እርስ በርስ ይፋለማሉ። ከዋንጫ ፉክክሩ ከተንሸራተተ የሰነባበተው ሀዋሳ ከተማ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በአመዛኙ በወጣቶች የተገነባው ቡድኑ ሳምንት ሽረ ላይ ያስተናገደው የ 4-0 ሽንፈት ደግሞ ፍፁም ይልተጠበቀ ነበር። ወደ ጅማ አቅንቶ 1-0 የተረታው ሲዳማ ቡናም እንደተለመደው ከሜዳው ውጪ ያለድል በመመለሱ ከፉክክሩ ገሸሽ እያለ ወደ አራተኛነት ዝቅ እንዲል ሆኗል። በመሆኑም ከሀዋሳም በላይ የጨዋታው ውጤት ለሲዳማ አስፈላጊ ነው።

ከሽንፈት ከመመለሳቸው ባለፈ በአጨዋወታቸው ተገማችነት የሚመሳሰሉት ሁለቱ ቡድኖች ነገም ተመሳሳይ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይገመታል። ቀጥተኛ አጨዋወትን የሚመርጡት እና ከመስመር ተመላላሾቻቸው በሚነሱ ኳሶች ጥቃት የሚሰነዝሩት ሀዋሳ ከተማዎች ገብረመስቀል ዱባለን በጉዳት ሲያጡ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ደግሞ ከቅጣት ይመለስላቸዋል። አሁንም የመስመር አጥቂዎቸው ፍጥነት ዋነኛ መተማመኛቸው የሆነው ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ መሣይ አያኖ ፣ ዮናታን ፍሰሀ እና ወንድሜነህ ዓይናለምን ከጉዳት አጥቂው መሀመድ ናስርን ከሆድ ህመም መልስ አገግመው ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆነውላቸዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ ለ19 ጊዜያት ከተገናኙባቸው ጨዋታዎች ስድስቱ በሲዳማ አምስቱ ደግሞ በሀዋሳ አሸናፊነት ሲጠናቀቁ 8 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። ሀዋሳ 19 ጎሎች ሲያስቆጥር ሲዳማ 22 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል።

– ሀዋሳ ላይ 12 ጨዋታዎችን ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች ስድስቱን አሸንፈው በሦስቱ ሲሸነፉ በቀሪዎቹ ሦስቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

– በሜዳቸው ሽንፈት ካልገጠማቸው ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሲዳማ ሀዋሳ ላይ 11 ጨዋታዎችን አድርጎ ስምንቱን በድል ሲወጣ በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎችም ነጥብ መጋራት ችሏል።

ዳኛ

– ሀዋሳን ከአባ ጅፋር ፣ ቡና እና ድቻ ሲዳማን ደግሞ ከጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ጋር ያጫወተው ኃይለየሱስ ባዘዘው ይህን ጨዋታ የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ኃይለየሱስ በእስካሁኖቹ ስምንት ጨዋታዎች 16 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲያሳይ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን የሰጠ ሲሆን አንድ ጊዜ ደግሞ ሁለተኛ የቢጫ ካርድን መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

አዲስዓለም ንጉሴ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – ታፈሰ ሰለሞን – ሄኖክ ድልቢ– ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ደስታ ዮሀንስ

አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ

ሲዳማ ቡና ( 4-3-3)

መሳይ አያኖ

ግሩም አሰፋ – ፈቱዲን ጀማል – ዳግም ንጉሴ – ሚሊዮን ሰለሞን

ወንድሜነህ ዓይናለም –ዮሴፍ ዮሐንስ – ግርማ በቀለ

ሐብታሙ ገዛኸኝ – መሐመድ ናስር – አዲስ ግደይ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡