ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

በድሬዳዋ እና ድቻ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ጉዳዮች አንስተናል።

በድሬዳዋ ስታድየም የሚደረገው ይህ ጨዋታ ተጋጣሚዎቹ በተለይም ደግሞ ወላይታ ድቻ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ወሳኝ ይሆናል። ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ጎንደር ላይ ሽንፈት አስተናግደው የተመለሱት ድሬዳዋ ከተማዎች ነጥባቸውን ከ30 በላይ በማሳለፍ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ለመጠጋት ወደ አሸናፊነት መመለስ ይጠበቅባቸዋል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ በማሳካቱ ምክንያት ተከታዮቹ የደረሱበት ወላይታ ድቻ ደግሞ በቀጣይ ጨዋታዎች ወደ አደጋ ላለመግባት የግድ ደረስንብህ እያሉት ያሉትን መከላከያ እና ደቡብ ፖሊስን መራቅ ይኖርበታል።

ከራምኬል ሎክ አለማገገም በቀር በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የሌላቸው ድሬዎች በዋነኝነት ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ተጋጣሚያቸውን እንደሚፈትኑ ይጠበቃል። ፀጋዬ አበራ እና አብዱልሰመድ ዓሊን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው ወላይታ ድቻ በበኩሉ ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ እንደሚኖረው ሲጠበቅ ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ መሆኑም ታውቋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ እስካሁን በተገናኙባቸው ሰባት ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ ድል ቀንቶት አያውቅም። ሦስቱ ጨዋታዎች በድሬዳዋ አሸናፊነት ሲጠናቀቁ ቀሪዎቹ የአቻ ውጤት ተመዝግቦባቸዋል። በጨዋታዎቹ ድሬዎች ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ድቻዎች ደግሞ ሁለት ግቦች ብቻ አሏቸው።

– ድሬዳዋ ከተማ ከተማ ሜዳው ላይ 11 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን አራት የሽንፈት ፣ አምስት የድል ፣ ሁለት ደግሞ የአቻ ውጤቶችን አስመዝግቧል።

– ከሶዶ በወጣባቸው 12 ጨዋታዎች ምንም ድል ያላሳካው ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርቶ የተመለሰውም አምስት ጊዜ ብቻ ነበር።

ዳኛ

– ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ትመራዋለች ። አርቢትሯ ባህር ዳር እና መቐለ እንዲሁም ሀዋሳ እና ጊዮርጊስ ካደረጓቸው ጨዋታዎች በኋላ የምትመራው ሦስተኛዋ ጨዋታ ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ (4-2-3-1)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – በረከት ሳሙኤል – ሳሙኤል ዮሀንስ

ፍሬድ ሙሸንዲ – ሚኪያስ ግርማ

ኤርሚያስ ኃይሉ – ኤልያስ ማሞ – ረመዳን ናስር

ኢታሙና ኬይሙኒ

ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)

መኳንንት አሸናፊ

እሸቱ መና – ደጉ ደበበ – ዐወል አብደላ – ሄኖክ አርፌጮ

በረከት ወልዴ

ፀጋዬ አበራ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ቸርነት ጉግሳ

ባዬ ገዛኸኝ – አላዛር ፋሲካ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡