ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ሀዋሳ ከተማ

የዛሬ ቅድመ ዳሰሳችን ቀዳሚ ትኩረት በሆነው የአባ ጅፋር እና ሀዋሳ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በሜዳው በሰባት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደው ጅማ አባ ጅፋር እና በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት የተሳነው ሀዋሳ ከተማ ነገ 09፡00 ላይ በጅማ ስታድየም ይገናኛሉ። ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ከወልዋሎ ነጥብ ተጋርተው የተመለሱት ጅማዎች ድል ከቀናቸው ነጥባቸውን ከ40 በላይ ካደረሱት የሊጉ ሦስት ክለቦች ዙሪያ የመሰለፍ ዕድል ይኖራቸዋል። ወገብ ላይ የመጨረስ አዝማሚያ እያሳዩ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በሁለተኛው ዙር ከአንድ ጊዜ በላይ ማግኘት ያልቻሉትን ድል ካሳኩ ሦስት ያህል ደረጃዎችን የማሻሻል አጋጣሚው ሊፈጠርላቸው ይችላል።

ግብ ጠባቂያቸው ዳንኤል አጃዬ ከፍቃድ ያልተመለሰላቸው ጅማዎች እንደ ሳምንቱ ሁሉ ከብሽሽት ጉዳት ያላገገመው አጥቂያቸው ማማዱ ሲዲቤን ተጠባባቂ አድርገው ጨዋታውን እንደሚጀምሩ ይጠበቃል። ሆኖም የአጥቂውን ብቁ አለመሆን እና ከሜዳ ውጪ መጫወቱን ተከትሎ በአንድ አጥቂ የወልዋሎውን ጨዋታ የጀመረው ቡድኑ ኋላ ላይ ባደረጋቸው ለውጦች የተሻለ መንቀሳቀሱ ነገ በተለመደው የ4-4-2 አሰላለፉ በመመለስ እና በዋነኝነት የማጥቃት ባህሪ ላላቸው አማካዮቹ ቅድሚያ በመስጠት እንደሚቀርብ ይጠበቃል። በዚህም ከዋለልኝ ገብሬ እና መስዑድ መሀመድ አንዳቸው ጨዋታውን የመጀመር ዕድል ሲኖራቸው ጅማ በኳስ ቁጥጥር ላይ በመመስረት ወደ መስመር አማካዮቹ አመዝኖ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር የማጥቃት አማራጭን ይዞ እንደሚገባ ይገመታል።

አዳማ ላይ የመጨረሻ ድሉን ካገኘ በኋላ በተከታታይ ለሦስት ጨዋታዎች ከአንድ ነጥብ ሌላ ካለማሳከቱ በላይ ሀዋሳ ከተማ ግብ ማስቆጠር አለመቻሉ ትልቁ ራስ ምታቱ ነው። ከዚህ አለፍ ሲልም ከ17ኛው ሳምንት በኋላ ከአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቹ ግብ አለማግኘቱ ለቡድኑ የጅማ ጉዞ ትልቅ ክፍተቱ ነው። በመሆኑም በጨዋታው ድፍረት የተሞላበት የተጨዋቾች ቅያሪ እና ተገማች ከሆነው የቡድኑ የመስመር ተመላላሾች እንቅስቃሴ ያለፈ ሁነኛ የማጥቃት መንገድ ከአሰልጣኞቹ ይጠበቃል። ነገር ግን የታፈሰ ሰለሞን ክለቡ ባስተላለፈበት  የዲሲፕሊን ቅጣት ምክንያት አለመኖር እንዲሁም የገብረመስቀል ዱባለ ከጉዳት አለመመለስ ሲታይ ደግሞ አዲስ ነገር ላይኖር እንደሚችል የሚጠቁም ነው። በጥቅሉ ግን የተጋጣሚውን የመስመር ጥቃት መመከት ላይ ያተኮረ እና ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሰጠ አቀራረብ ከሀይቆቹ ይጠበቃል። ለዚህም የቁልፉ ተከላካይ መሳይ ጻውሎስ ከጉዳት መመለስ ለቡድኑ ጥሩ ተስፋ ሲሆን በአንፃሩ የተከላካይ አማካዩ ሄኖክ ድልቢ ደግሞ ወደ ጅማ አላመራም፡፡

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ጅማ አባ ጅፋር አምና ወደ ሊጉ ሲያድግ ሀዋሳ ከተማን 2-0 በመርታት ጨዋታ ነበር ገዞውን የጀመረው። ሁለተኛው ዙር ላይ ግን ሀዋሳ በሜዳው 1-0 በማሸነፍ ቻምፒዮኖቹን በሁለተኛ ዙር ድል ያደረገ ብቸኛው ክለብ መሆን ሲችል ዘንድሮም የ3-1 ድልን አሳክቷል።

– ጅማዎች በሜዳቸው 11 ጨዋታዎችን ሲያደርጉ ሽንፈት ሳይገጥማቸው ስድስቱን በድል አምስቱን ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። ባለፉት ሰባት የሜዳ ላይ ጨዋታቸውም መረባቸውን አላስደፈሩም።

– ሀዋሳ ከተማ ካደረጋቸው 11 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ስድስት ጊዜ ሲሸነፍ ሦስቴ ነጥብ መጋራት የቻለ ሲሆን ሁለት ጊዜ ደግሞ በድል ተመልሷል።

ዳኛ

– ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ መሪነት ይከናወናል። አርቢትሩ እስካሁን 11 ጨዋታዎችን በመዳኘት 44 የቢጫ ካርዶችን ሲመዝ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን የሰጠ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ የዳኛቸው ሁለት ጨዋታዎችም ጅማን ከሲዳማ ሀዋሳን ደግሞ ከአዳማ ያገናኙ ነበሩ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባጅፋር (4-4-2)

ዘሪሁን ታደለ

ዐወት ገ/ሚካኤል – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ ዓታሮ

ዲዲዬ ለብሪ – መስዑድ መሀመድ –ይሁን እንዳሻው – አስቻለው ግርማ

ኦኪኪ አፎላቢ – ብሩክ ገብረአብ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ወንድማገኝ ማዕረግ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – አክሊሉ ተፈራ – ምንተስኖት አበራ – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ደስታ ዮሀንስ

አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ