ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ መቐለ 70 እንደርታ

በዚህ ሳምንት ከሚደረጉት ጨዋታዎች ውስጥ እጅግ ተጠባቂ የሆነውን እና በሁለት የዋንጫ ተፎካካሪ ክለቦች መካከል የሚደረገውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከሁለተኛው ዙር መጀመር በኃላ አራት ሽንፈቶች የገጠሟቸው ሲዳማዎች የሊጉን መሪ በማሸነፍ ወደ ዋንጫው ፉክክር ይበልጥ ለመጠጋት አስበው ይህን ጨዋታ እንደሚያደርጉ እሙን ነው። በመስመር በሚደረጉት ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች እና ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት የሚሞክሩት ሲዳማ ቡናዎች ተጋጣሚያቸው ወደ መሀል ሜዳ ቀርቦ ይከላከላል ተብሎ ስለማይጠበቅ የመስመር አጨዋወትን ሁነኛ የማጥቃት መሳርያቸው ለማድረግ አልመው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፉት ጨዋታዎች መሐመድ ናስርን በጉዳት ማጣታቸውን ተከትሎ በሀብታሙ ገዛኸኝ እና አዲስ ግደይ ላይ የተንጠለጠለ የማጥቃት አጨዋወት ለመከተል ተገደው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በዚህ ጨዋታ አንጋፋው አጥቂ ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ጥሩ አማራጭ የሚፈጥርላቸው ይሆናል። ከዚህ ባለፈ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች የመከላከል ባህሪ ባላቸው ተጫዋቾች የተገነባ የአማካይ ክፍል የነበረው ቡድኑ ነገም በተመሳሳይ የተጫዋቾች ምርጫ የሚፀና ከሆነ በኳስ ቁጥጥር ረገድ ጥሩ የሆነውን የመቐለ የአማካይ ክፍልን ለመብለጥ ሊቸገር ይችላል። ሲዳማ ቡናዎች ግብ ጠባቂያቸው ፍቅሩ ወዴሳን  በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይጠቀሙም።

ባለፉት ጨዋታዎች እንደተጋጣሚያቸው የጨዋታ አቀራረብ አጨዋወታቸው ላይ መጠነኛ ለውጥ እያደረጉ የቀጠሉት መቐለዎች በዚህ ጨዋታ ጥብቅ መከላከል ላይ የተመሰረተ የመልሶ ማጥቃትን ይዘው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የያሬድ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ጠንካራው የአጥቂ ጥምረት ላይ ለውጥ ካደረጉ በኃላ በተወሰኑ ጨዋታዎች የማጥቃት ክፍላቸው ሳስቶ የነበረው ምዓም አናብስት ነገ ኦሴይ ማውሊን በጉዳት ስለማያገኙ የያሬድ እና አማኑኤልን ጥምረት የሚመልስ ይመስላል። በአሰላለፍ ደረጃም ለውጥ በማድረግ 4-2-3-1 እና 4-4-2(ጠባብ) እያፈራረቁ የተጠቀሙት ምዓም አናብስት በነገው ጨዋታ ያለፉት ሁለት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች የተከተሉትን የመስመር አጨዋወት የተሻለ ለማሳካት እና የተጋጣሚያቸው ጠንካራ የመልሶ ማጥቃት መመከት የሚያስችላቸውን የ4-2-3-1 አደራደር መርጠው ይገባሉ ተብሎ ይገመታል።

ከዚህ በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከብዙ ጊዜ በኃላ የተከላካይ ክፍላቸውን ወደ መሀል ሜዳ አስጠግተው መጫወትን የመረጡት ምዓም አናብስት ተጋጣሚያቸው ፈጣኖች እና ከተከላካይ ጀርባ የሚገኘውን ክፍት ቦታ መጠቀም የሚችሉ አጥቂዎችን የያዘ ቡድን እንደመሆኑ ተከላካዮቹ ወደ ሳጥናቸው የቀረበ የቦታ አያያዝ እንደሚኖራቸው ይታሰባል። በእንግዶቹ በኩል አቼምፖንግ አሞስ እና ሰሞነኛ ተወዳሹ ኦሴይ ማውሊ በጉዳት አያሰልፉም አሌክስ ተሰማም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች በሊጉ የተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች በሙሉ በመሸናነፍ የተጠናቀቁ ነበሩ። መቐለዎች በሜዳቸው አምና የ1-0 ዘንድሮ ደግሞ የ3-1 ድል ሲያስመዘግቡ ሲዳማ ቡና አምና በሜዳው 2-1 ማሸነፍ ችሏል።

– በሜዳቸው ሽንፈት ካልገጠማቸው ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሲዳማ ሀዋሳ ላይ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ ዘጠኙን በድል ሲወጣ በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎችም ነጥብ መጋራት ችሏል።

– መቐለ 70 እንደርታ ዘጠኝ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን ሲያከናውን በመጀመሪያ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ አቻ በመውጣት ከዚያም ሦስት ተከታታይ ድሎችን ቢያስመዘግብም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎቹ ደግሞ ተሸንፏል።

ዳኛ

– ጨዋታው ዘንድሮ ለኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ዘጠነኛ ጨዋታው ይሆናል። አርቢትሩ በእስካሁኖቹ ስምንት ጨዋታዎች 29 የማስተጠንቀቂያ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ግሩም አሰፋ – ፈቱዲን ጀማል – ዳግም ንጉሴ – ሚሊዮን ሰለሞን

ወንድሜነህ ዓይናለም – ዮሴፍ ዮሃንስ – ግርማ በቀለ

ሀብታሙ ገዛኸኝ – መሐመድ ናስር – አዲስ ግደይ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፍሊፕ ኦቮኖ

ስዩም ተስፋዬ – ክዌኪ አንዶህ – አሚኑ ነስሩ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ሀይደር ሸረፋ – ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ – ሳሙኤል ሳሊሶ

ያሬድ ከበደ – አማኑኤል ገብረሚካኤል