ከፍተኛ ሊግ ሀ | ሰበታ ነጥብ ሲጥል ለገጣፎ አሸንፏል


የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 17ኛ ሳምንት የምድብ ሀ ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተከናውነው መሪው ሰበታ ነጥብ ሲጥል ተከታዩ ለገጣፎ አሸንፎ ልዩነቱን አጥብቧል።

ከሜዳው ውጪ አቃቂ ቃሊቲን የገጠመው ሰበታ ከተማ ያለ ጎል ጨዋታውን አጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ሰበታ ከተከታዩ ለገጣፎ የነበረው ልዩነት ወደ አንድ ጠቧል።

ለገጣፎ ለገዳዲ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል ወሎ ኮምቦልቻን 1-0 በማሸነፍ ሰበታ አንገት ስር መተንፈሱን ቀጥሏል። ዳዊት ቀለመወርቅ በ90ኛው ደቂቃ ወሳኛን የማሸነፍያ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ደሴ ከተማ መሻሻሉን በመቀጠል በዚህም ሳምንህ ድል አስመዝግቧል። አክሱም ከተማን ያስተናገደው ደሴ በሁለተኛው ዙር ጎሎችን እያስቆጠረ በሚገኘው በድሩ ኑርሁሴን የ75ኛ ደቂቃ ጎል 1-0 አሸንፏል።

በዕለተ ቅዳሜ ኤሌክትሪክ በገላን ከተማ 1-0 ተሸንፎ ከፉክክሩ ርቋል። የገላንን ብቸኛ የማሸነፍያ ጎል በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃ ያስቆጠረው እሸቱ ጌታሁን ነው።

አውስኮድ በሁለተኛ ዙር እያሳየ ባለው መነቃቃት ቀጥሎ ወልዲያን ከሜዳው ውጪ 2-0 አሸንፏል። ሚካኤል ጆርጅ በ25ኛው ደቂቃ ቀዳሚውን ሲያስቆጥር ዮናስ ግርማ ለእረፍት ሊወጡ ሁለት ደቂቃ ሲቀር ተከታዩን ጎል ማስቆጠር ችሏል። ግርጌ ላይ የሚገኘው አውስኮድ ነጥቡን 13 በማድረስ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ትግሉን ቀጥሏል።

ቡራዩ ከተማ በሜዳው ፌዴራል ፖሊስን 2-0 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያቃርበውን ሦስት ነጥብ አግኝቷል። ቢኒያም ጌታቸው በ5ኛው ደቂቃ ቀዳሚውን ሲያስቆጥር ቃለአብ ጋሻው በ30ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን አክሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡