ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ፋሲል ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

የፋሲል እና ጅማ ጨዋታ ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት ነው።

በአፄ ፋሲለደስ ስታድየም የሚደረገው ጨዋታ የአምናውን ቻምፒዮን እና የዘንድሮውን የዋንጫ ተፎካካሪ የሚያገናኝ ይሆናል። አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን ያስመዘገበት አፄዎቹ ከመሪው ጋር ያላቸውን ነጥብ ወደ ሁለት ዝቅ በማድረግ ለዋንጫው የሚያደርጉትን ጉዞ አስቀጥለዋል። ከወልዋሎው ጨዋታ በኋላም ነገም እስካሁን ባልተሸነፉበት ሜዳቸው ላይ መጫወታቸው የሚጨምርላቸው ተነሳሽነትም ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል። ከስድስት ጨዋታዎች አምስቱን ማሸነፉን ተከትሎ ወደ ፉክክሩ ቀርቦ የነበረው አባ ጅፋር ባለፉት ደግሞ ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ በማሳካቱ ከአምስተኛ ደረጃ ከፍ እንዳይል ሆኖ ለጨዋታው ደርሷል።

ሜዳቸው ላይ ባደረጓቸው የተወሰኑ ጨዋታዎች በሦስት ተከላካዮች የሚጀምር አሰላለፍ በመጠቀም የማጥቃት ኃይላቸውን ጨምረው ሲጫወቱ የነበሩት ፋሲሎች በወልዋሎው ጨዋታ ወደ ተለምዷዊው 4-3-3 ተመልሰዋል። ይህም ነገም ተመሳሳይ አቀራረብ ሊኖራቸው እንደሚችል የሚጠቁም ነው። ከአሰላለፍ ምርጫቸው ውጪ ግን በበርካት ቅብብሎች ላይ ተመስርተው የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመያዝ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ በመቆየት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እንደሚሰነዝሩ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ ተጋጣሚያቸው በጉዳት ከሚያጣቸው ተጨዋቾች አንፃር ወደ ኋላ ሊያፈገፍግ መቻሉ ባለሜዳዎቹ በቀላሉ ክፍተቶችን እንዳያገኙ ሊያደርጋቸው ይችላል። ያም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ የማጥቃት ባህሪን በተላበሰው የሦስትዮሽ የአማካይ ክፍላቸውን ፈጠራ እና ፍጥነት በመጠቀም ወደ ግራ አዘንብለው እንደሚያጠቁ ይገመታል። በጨዋታው መጣባቸው ሙሉ ፣ ሰለሞን ሀብቴ እና ፀጋአብ ዮሴፍ ከጉዳት የመመለሳቸው ዜናም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለሚኖራቸው የማጥቃት ስትራቴጂ አጋዥ እንደሚሆን ሲታመን ሀብታሙ ተከስተ ግን አሁንም ጉዳት ላይ ነው።

ጅማ አባጅፋር አራት ቁልፍ የመጀመሪያ ተሰላፊዎቸንን ሳይዝ ወደ ጎንደር ማቅናቱ ጨዋታውን ይበልጥ የሚያከብድበት ጉዳይ ነው። ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጃዬ በተሰጠው ፍቃድ ወደ ኔዘርላንድ ካመራ በኋላ እስካሁን ባለመመለሱ ለነገው የማይደርስ ሲሆን መስዑድ መሀመድም በግል ጉዳይ ምክንያት አይኖርም። ከዚህ በተጨማሪ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዐወት ገሚከረኤል በሀዋሳው ጨዋታ ላይ በደረሰበት ጉዳት ነገ ቡድኑን የማያገለግል ሲሆን በተመሳሳይ በሀዋሳው ጨዋታ ላይ አደጋ ደርሶበት የነበረው ኦኪኪ አፎላቢም ወደ ጎንደር አልተጓዘም። በጅማ በኩል የተሰማው መልካም ዜና ያለፉትን ሦስት ሳምንታትን ከጉዳት ጋር እየታገለ የሚገኘው አጥቂው ማማዱ ሲድቤ ወደ ቀዳሚ ተሰላፉነት ሊመለስ መቻሉ ነው። በዚህም ምክንያት ቡድኑ የአሰላለፍ ለውጥ ሊያደርግ የሚችልበት ዕድል የሰፋ ሲሆን በራሱ ሜዳ ላይ ቆይቶ በመከላከል ለማማዱ ሲዲቤ ቀጥተኛ ኳሶችን በማሻገር ላይ ያመዘነ አጨዋወትን ሊከተል እንደሚችል ይገመታል። የመስዑድ መሀመድ እና ዐወት ገብረሚካኤል አለመኖርም ቡድኑ መሀል ላይ ተረጋግቶ ኳስ እንዳይዝ እና ከቀኝ መስመር በሙነሱ ጥቃቶች ወደ ፉት ገፍቶ እንዳይጫወት ሊያደርጉት ይችላሉ።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– የቅርብ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች አምና ጅማ ላይ ፋሲል 1-0 ያሸነፈ ሲሆን ሁለት ጊዜ ያለግብ ተለያይተዋል።

– በሜዳው ስምንት ድሎች እና አራት የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገበው ፋሲል ከነማ እስካሁን ሽንፈት አላገኘውም።

– ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳ ውጪ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች አራቴ በድል ሦስት ጊዜ ደግሞ በአቻ ውጤት ሲመለስ በአምስት ጨዋታዎች ተሸንፏል።

ዳኛ

– ጨዋታው ለተካልኝ ለማ ለስምንተኛ ጊዜ በመሀል ዳኝነት የተመደበበት ነው። ፋሲልን ከድቻ ጅማን ደግሞ ከሲዳማ እና መቐለ ጋር ያጫወተው አርቢትሩ እስካሁን 25 የቢጫ ካርዶችን ሲመዝ 2 የሁለተኛ ቢጫ ካርድ እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሀሰን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – ኤፍሬም አለሙ – ሱራፌል ዳኛቸው

ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ

ጅማ አባጅፋር (4-4-2)

ዘሪሁን ታደለ

ተስፋዬ መላኩ – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ

ዲዲዬ ለብሪ – ዋለልኝ ገብሬ – ይሁን እንዳሻው – አስቻለው ግርማ

ማማዱ ሲዲቤ – ብሩክ ገብረአብ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡