ሪፖርት | ወልዋሎ እና ወላይታ ድቻ አቻ ተለያይተዋል

ወልዋሎ እና ወላይታ ድቻን ያገናኘው የ25ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በአቻ ውጤት ፍፃሜው አገኝቷል።

ወልዋሎዎች በፋሲል ሽንፈት ከገጠመው ቡድናቸው እንየው ካሳሁን እና አብዱራሕማን ፉሴይኒን በደስታ ደሙ እና ሬችሞንድ አዶንጎ ተክተው ሲገቡ እንግዶቹ ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው በ23ኛ ሳምንት ድሬዳዋን ከገጠመው ቡድናቸው መኳንንት አሸናፊ፣ አንተነህ ጉግሳ እና ውብሸህ አለማየሁ በማስወጣት በታሪክ ጌትነት ፣ ተክሉ ታፈሰ እና ቸርነት ጉግሳ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

አሰልቺ እና በሙከራ ባልታጀበው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች እንግዶቹ የጦና ንቦች ተሽለው በመንቀሳቀስ ጥቂት የማይባሉ የግብ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። አብዱልሰመድ ዓሊ ከርቀት አክርሮ መቶ ወደ ውጭ በወጣበት ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በሙከራ ደረጃ የተሻሉ ቢኖሩም ብልጫቸው ለብዙ ደቂቃዎች መዝለቅ አልቻለም። በዚህም በመጀመርያው አጋማሽ ባየ ገዛኸኝ እና ዓብዱልሰመድ ዓሊ አንድ ሁለት ተቀባብለው ከፈጠሯት የግብ ዕድል ውጭ የተቀሩት ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት የተሞከሩ ሙከራዎች ነበሩ። ዓብዱልሰመድ ዓሊ በሁለት አጋጣሚዎች ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ያደረጋቸው ሙከራዎች ቡድኑ በመጀመርያው አጋማሽ ካደረጋቸው ሙከራዎች የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

በጨዋታው ዘግይተው ወደ ቅኝት የገቡት ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ጫና በፈጠሩባቸው ደቂቃዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም እንደተጋጣምያቸው ሁሉ ከሳጥን ውጭ አክረው ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጭ ይህ ነው የሚባል ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም ሬችሞንድ አዶንጎ በወላይታ ድቻ ተከላካዮች ስህተት ያገኛትን ኳስ በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ችግር ባያመክናት ኖሮ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ነበረች። ወልዋሎዎች ከላይ ከተጠቀሰች መከራ ውጭም በሶስት አጋጣሚዎች ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር በተለይም ፕሪንስ አክርሮ መቶ ሄኖክ አርፊጮ ተደርቦ ያወጣት ሙከራ እና አማኑኤል ጎበና ከርቀት መቶ ታሪኬ ጌትነት በቀላሉ ያዳናት ኳስ ከታዩት ሙከራዎች የተሻሉ ነበሩ።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የፉክክር መንፈስ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ የባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ብልጫ የታየበት ነበር። አፈወርቅ ኃይሉ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቶ ታሪኬ ጌትነት በድንቅ ብቃት በመለሰው ጥሩ ሙከራ ጨዋታውን የጀመሩት ወልዋሎዎች ጫና በፈጠሩባቸው የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ ሙከራዎች አድርገዋል።
በተለይም ተቀይሮ የገባው ዓብዱራሕማን ፉሴይኒ ከርቀት አክርሮ መቶ ታሪኬ ጌትነት በድንቅ ብቃት ያወጣት ሙከራ በቢጫ ለባሾቹ በኩል ወርቃማ ዕድል ነበረች።

ከሁለተኛው አጋማሽ መጀመር አንስቶ አፈግፍጎ መጫወት ምርጫቸው ያደረጉት የጦና ንቦች ከተጋጣምያቸው አንፃር ሲታይ ደካማ የማጥቃት አጨዋወት ቢከተሉም ጥቂት የግብ ሙከራዎች ከማድረግ ግን አልቦዘኑም። ከነዚህም ደጉ ደበበ እሸቱ መና ከመዓዝን ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ በመምታት ያደረጋት ሙከራ እና ባየ ገዛኸኝ በግል ጥረቱ ተጫዋቾች አልፎ ያደረጋት ወርቃማ ዕድል በእንግዶቹ በኩል አስቆጪ ሙከራ ነበረች። ከዚ በተጨማሪ ዓብዱልሰመድ ዓሊ ግብጠባቂው ዓብዱልዓዚዝ ኬታ አርቃለው ብሎ የመታት ኳስ ተደርቦ ኳሷ ወደ ግቡ ብታመራም ደስታ ደሙ ጎል ከመሆን አድኗታል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ደረጃቸው ማሻሻል አልቻሉም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡