ሪፖርት | መቐለ በሜዳው በሀዋሳ ተሸንፎ የሊጉን መሪነት አስረክቧል

በትግራይ ስታድየም በተደረገው የዛሬ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ የመቐለ 70 እንደርታን በሜዳው ያለመሸነፍ ጉዞ በመግታት ደረጃውን አሻሽሏል።

ባለሜዳዎቹ ባለፈው ሳምንት በሲዳማ ሽንፈት ከገጠመው ቡድናቸው ፍሊፕ ኦቮኖ ፣ ሀይደር ሸረፋ እና ክዌኩ አንዶህን በሶፈንያስ ሰይፈ ፣ አሚኑ ነስሩ እና ያሬድ ብርሃኑ ተክተው ሲገቡ ሀዋሳዎች ከጅማ አባ ጅፋር ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ዳንኤል ደርቤ እና ወንድማገኝ ማዕረግን በአስጨናቂ ሉቃስ እና መስፍን ታፈሰ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ፈጣን የማጥቃት አጨዋወት የጀመረው ጨዋታው በመጀመርያው አጋማሽ በርካታ የግብ ሙከራዎች ፣ ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች እና ልብ አንጠልጣይ ሁነቶች የታዩበት ነበር። በጨዋታው በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሜዳውን ስፋት በአግባቡ ለመጠቀም የሞከሩት መቐለዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የሀዋሳ ተከላካዮች ትኩረት ማጣትን ተጠቅመው ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በተለይም አማኑኤል ገብረሚካኤል የሀዋሳ ተጫዋቾች መዘናጋትን አይቶ ብቻውን ተነጥሎ ለነበረው ያሬድ ብርሃኑ የወረወረውን የእጅ ውርወራ አማካዩ ይዞ በመግባት ቢመታም ላውረንስ ላርቴ እንደምንም ተደርቦ አውጥቶበታል።

ከዚህ ሙከራ ውጪም አማኑኤል ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ እና ዮናስ ገረመው አሻምቶት ያሬድ ከበደ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት የወጣው እጅግ ለግብ የቀረቡ የባለሜዳዎቹ ሙከራዎች ናቸው። በሌላ አጋጣሚም በያሬድ ብርሃኑ እና ሚካኤል ደስታ ጥሩ ተግባቦት የተፈጠረችውን ጥሩ ሙከራ ሶሆሆ ሜንሳህ ወጥቶ ባያድናት 70 እንደርታዎቹን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።


በተከላካይ ክፍላቸው ስህተቶች ምክንያት በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጥቂት አለመረጋጋት የተስተዋለባቸው ሀይቆቹ ዘግይተው ወደ ጨዋታው ቅኝት ቢገቡም በተለይም በመጨረሻዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ጥሩ ተንቀሳቅሰው ግብም ማስቆጠር ችለዋል። አዳነ ግርማ ከቅጣት ምት አሻምቶት ደስታ ዮሃንስ በግንባር ባደረገው ሙከራ ወደ ባለሜዳዎቹ ግብ ክልል መድረስ የጀመሩት ሀዋሳዎች የመሀል ሜዳ ብልጫ መውሰድ ባይችሉም የመስመር አጨዋወታቸው እና ወደ ግዙፉ አጥቂ የሚላኩት ረጃጅም ኳሶቻቸው በጣም ውጤታማ ነበሩ። በዚህ አኳዃንም ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎችን አድርገዋል። ከነዚህም እስራኤል እሸቱ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ የመታው እና ራሱ እስራኤል በመቐለ ተከላካዮች ስህተት ያገኘው ኳስ ተጠቅሞ ሞክሮ ሶፈንያስ ሠይፈ በድንቅ ብቃት ያወጣው በዕንግዶቹ በኩል ከተፈጠሩት የግብ ዕድሎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። በ35ኛው ደቂቃም መስፍን ታፈሰ መሳይ ጻውሎስ በጥሩ ሁኔታ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ በመምታት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

የምዓም አናብስት ሙሉ ብልጫ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ የሀዋሳ ከተማዎች እጅግ ጠንካራ የመከላከል ብቃትንም አስመልክቶናል። ከመጀመርያው አጋማሽ አቀራረባቸው ወጣ ብለው በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን በተደጋጋሚ የደረሱት 70 እንደርታዎች በርካታ የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩም ጠንካራውን ሀዋሳ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። ሀዋሳዎች ብቸኛ አጥቂያቸውን ጨምሮ ወደ ራሳቸው ግብ ክልል በእጅጉ ማፈግፈጋቸው እና በመስመሮች መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበባቸው ምክንያት በተቀራኒ ሜዳ ቁልፍ የማጥቅያ መንገዶች ያጡት መቐለዎች አብዛኞቹን ሙከራዎቻቸው ከርቀት የተደረጉ ነበሩ። ከነዚህም ውስጥ ተቀይሮ የገባው ሀይደር ሸረፋ በሁለት አጋጣሚዎች ከርቀት የሞከራቸው እና ጋብርኤል አህመድ ከሳጥኑ ጠርዝ ያደረገው ሙከራ በተሻለ መልኩ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። ከዚህ ሌላም በሶሆሆ ድንቅ ብቃት የመከነው የአማኑኤል ገብረሚካኤል ወርቃማ ሙከራ እና የሚካኤል ደስታ ሌላ ሙከራ መቐለዎችን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ። ከሁሉም በላይ ግን በጥማሪ ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል ያመከናት ፍፁም ቅጣት ምት መቐለዎችን አቻ ማድረግ ትችል የነበረች በመሆኗ ለቡድኑ የምታስቆጭ ሆና አልፋለች።

ውጤቱ በዚህ መልኩ መጠናቀቁን ተከትሎ ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ከረጅም ጊዜ በኃላ ከሊጉ መሪነት ሲወርዱ ሃዋሳ ከተማዎች ሦስተኛ የሜዳ ውጪ ድላቸውን አስመዝግበዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡