ለዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ከፕሪምየር ሊጉ ሁለት ተጫዋቾች ተጠርተዋል

የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሴባስቲያ ድሳብር ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት የመጀመርያ 27 ተጫዋቾች ምርጫን ሲያከናውኑ ሁለት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾችን በዝርዝሩ ውስጥ አካተዋል።

የአዳማ ከተማው ሮበርት ኦዶንካራ በስብስቡ ውስጥ ከተካተቱ አራት ግብ ጠባቂዎች አንዱ ነው። ሮበርት የመጨረሻ ሦስት ግብ ጠባቂዎች ውስጥ ለመካተት ከቡድኑ አምበል ዴኒስ ኦኒያንጎ በተጨማሪ ከቻርለስ ሉክዋጎ እና ጀማል ሳሊም ጋር ፉክክር ይጠብቀዋል።

ሌላው በ27 ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ የተካተተው ክሪዚስቶም ንታምቢ ነው። የኢትዮጵያ ቡናው ተጫዋች በአማካይ እና ተከላካይ ስፍራ ላይ መጫወት መቻሉ በመጨረሻ ስብስብ ውስጥ እንዲካተት ሊያደርገው ይችላል።

በምድብ ሀ ከአዘጋጇ ግብፅ፣ ዚምባብዌ እና ዲሪ. ኮንጎ ጋር የተደለደሉት ክሬንሶች ለአፍሪካ ዋንጫው ዝግጅት ከአራት ቀናት በኋላ ወደተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መዲና አቡዳቢ የሚያቀኑ ሲሆን ሁለቱ ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ክለቦቹ እንዲለቋቸው ከዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን (FUFA) ለኢትዮጵያ አቻው ጥያቄ ማቅረቡን ፌዴሬሽኑ በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል። በዚህም ምክንያት ተጫዋቾቹ የብሔራዊ ቡድኑን ዝግጅት ከተቀላቀሉ የመጨረሻዎቹ አራት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች የሚያልፋቸው ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡