ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን አሸንፎ ከመሪዎቹ ያለውን ልዩነት ዝቅ አድርጓል

ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በአስቻለው ታመነ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት ጎሎች በባለሜዳዎቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ከተጠቀመው የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በኢሱፍ ቡሩሀና ፣ ታደለ መንገሻ እና ጉዳት በገጠመው በኃይሉ አሰፋ ምትክ ሳላዲን በርጌቾ ፣ ሀምፍሬይ ሚዬኖ እና ከጉዳት የተመለሰው አቤል ያለውን ተጠቅሟል። በሜዳቸው አዳማን ያሸነፉት ድሬዳዋዎችም ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች በረከት ሳሙኤል እና ሳሙኤል ዮሃንስን በያሬድ ዘውድነህ እና ፍቃድ ላይ በሚገኘው ዘነበ ከበደ ተክተዋል።

ጨዋታው ቡድኖቹ በተመጣጠነ ሁኔታ ኳስ በመያዝ ያደርጉት በነበረው የተቀዛቀዘ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ የጀመረ ነበር። ነገር ግን አልፎ አልፎ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት ለመጣል የሚሞክሩት ጊዮርጊሶችም ሆኑ በቅብብል እስከመጨረሻው ለመዝለቅ ይጣሩት ድሬዳዋዎች ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል የሚደርሱት በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ሆኗል። 11ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ወልዴ ኤርሚያስ ኃይሉ ከአብዱከሪም መሀመድ ቀምቶ የሰጠውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ለምንያህል ተሾመ አሳልፎለት የአማካዩ ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ከወጣ በኋላ ግን ጨዋታው በመጠኑ ተነቃቅቶ ታይቷል። 15ኛው ደቂቃ ላይም አሜ መሀመድ ከቀኝ መስመር ያሳለፈለትን ኳስ ሪቻርድ አርተር በያዘበት ቅፅበት በበረከት ሳሙኤል ጥፋት ተሰርቶበታል በማለት የመሀል ዳኛው አማኑኤል ኃይለስላሴ የሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አስቻለው ታመነ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ቀሪዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ግን ጨዋታው ወደ ጀመረበት ቀዝቃዛ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ የተመለሰባቸው ነበሩ። 23ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን ናስር ከርቀት ካደረገው ቀለል ያለ የርቀት ሙከራ በኋላ ተጋጣሚዎቹ ሌላ የተሻለ የግብ አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ድሬዎች እጅግ ወደ መሀል የጠበበው እና የመስመር ተከላካዮቻቸውን ያላሳተፈው የማጥቃት መንገዳቸው በቀላሉ በጊዮርጊስ ተከላካዮች ይበላሽ ነበር። ወደ ብቸኛው አጥቂያቸው ሀብታሙ ለማሳለፍ የሞከሯቸውም ቀጥተኛ ኳሶችም አጥቂውን ከግብ ጠባቂ ጋር ማገናኘት የቻሉ አልነበሩም። በብዛት ወደ ቀኝ አዘንብለው ፈጣን ጥቃት ለመሰንዘር ይሞክሩ የነበሩት ጊዮርጊሶችም የፍፁም ቅጣት ምቱን ካስገኘላቸው ጥቃት ውጪ ሌላ አስፈሪ እንቅስቃሴ አላደረጉም። ቡድኖቹ ያገኟቸው የነበሩ የማዕዘን ምቶችም ቢሆኑ የሙከራ ምንጭ መሆን ሳይችሉ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

የሁለተኛው አጋማሽ አጀማመር ከመጀመሪያው የተለየ አልነበረም። የመጀመሪያው ሙከራም ከ18 ደቂቃዎች በኋላ ረመዳን ከርቀት መቶት ማታሲ በቀላሉ ያዳነው ኳስ ነበር። በአጨዋወት ደረጃ 57ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በገባው ታደለ መንገሻ ረዘም ያሉ ኳሶች በቶሎ ወደ መስመር አጥቂዎቻቸው ያሻግሩ የነበሩት ጊዮርጊሶች ቀጥተኝነት ሲታይባቸው ድሬዎች ግን በተመሳሳይ በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አጨዋወታቸው ቀጥለዋል። 68ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገናናው ረጋሳ ከተቀማ ኳስ በቀኝ አቅጣጫ ያሳለፈለትን ሳጥን ውስጥ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚም የተሻለው ሙከራቸው ነበር። 70ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም በቀኝ በኩል ከታደለ ተቀብሎ ወደ ውስጥ የመታው ኳስ በድሬው የመሀል ተከላካይ አንተነህ ተስፋዬ በእጅ ተነክቷል የሚለው የዳኞች ውሳኔ ከእንግዶቹ በዙ ተቃውሞ ቢገጥመውም አስቻለው ታመነ የፍፁም ቅጣት ምቱን ወደ ግብ ቀይሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።

ከዚህ ውጪ በ76ኛው ደቂቃ አቤል ያለው ከታደለ የደረሰውን ኳስ በግራ የሳጥኑ ክፍል ገብቶ ከሞከረው ኃይል የሌለው ኳስ እና ከጋዲሳ መብራቴ የጭማሪ ደቂቃ የርቀት ሙከራ ውጪ ጨዋታው ሌላ አደጋ የሚፈጥር እንቅስቃሴ ሳይታይበት እጅግ አሰልቺ በሆነ መንገድ ቀጥሎ ፍፃሜውን አግኝቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳካው ድል ከሦስቱ መሪዎች ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ስድስት ነጥብ ዝቅ ሲያደርግ ተሸናፊው ድሬዳዋ በነበረበት 10ኛ ደረጃ ላይ ቀርቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡