በዓምላክ ተሰማ በመራው ጨዋታ ዛማሌክ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል

በ2018/19 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመልስ ጨዋታ ዛማሌክ የሞሮኮው አር ኤስ በርካኔን አስተናግዶ በመለያ ምቶች በማሸነፍ ከ16 ዓመታት በኋላ የአህጉራዊ ዋንጫ ረሀቡን አስታግሷል።

ባሳለፍነው ሳምንት ሞሮኮ ላይ በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ በርካኔ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል 1-0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። በበዓምላክ ተሰማ ዳኝነት የተከናወነው የመልሱ ጨዋታ በአሌክሳንድሪያው ቦሮግ አል አረብ ስታድየም እሁድ ምሽት ሲከናወን በ54ኛው ደቂቃ ላርቢ ናጂ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጁ በመንካቱ በVAR ተረጋግጦ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት መሐመድ አላ አስቆጥሮ ዛማሌክ በድምር ውጤት አቻ እንዲሆን አድርጓል።

ጨዋታው በዛማሌክ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ በተሰጡ የመለያ ፍፁም ቅጣት ምቶች ዛማሌኮች ሁሉንም ሲያስቆጥሩ በበርካኔ በኩል ሐምዲ ላቸር አምክኖ ነጭ ለባሾቹ አሸናፊ መሆን ችለዋል።

አምስት ጊዜ የቻምፒየንስ ሊግ፣ ሶስት ጊዜ የሱፐር ካፕ እንዲሁም የቀድሞው ካፕ ዊነርስ ካፕን አንድ ጊዜ ማሳካት የቻለው የግብፁ ታላቅ ክለብ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫን ሲያነሳ ይህ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ነው። የዋንጫው ባለቤት ዛማሌክ 1.25 ሚሊዮን ዶላር ሲሸለም ተሸናፊው በርካኔ 625 ሺህ ዶላር ማግኘት ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡