የግል አስተያየት | የደደቢት የውድድር ዓመቱ ጉዞ ሲዳሰስ

የግል አስተያየት – በማቲያስ ኃይለማርያም

ባለፉት ዓመታት በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረውን ስብስብ አፍርሰው አዲስ ቡድን በመገንባት ለውድድር የቀረቡት ደደቢቶች ባለፈው ሳምንት ከሊጉ የመውረዳቸው እርግጥ መሆኑ ይታወሳል።

በትንሽ በጀት አዲስ ቡድን ገንብተው ወደ ውድድር እንደሚቀርቡ ካስታወቁ በኋላ የብዙዎች ትኩረት የሳቡት ሰማያዊዎቹ ከሜዳ ውጭ ባሉ በርካታ የፋይናንስ ችግሮች ታጅበው ውድድራቸው ማድረጋቸው በሜዳ ውስጥ ብቃታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢያሳርፍባቸውም የቡድን አመራሮች እና አሰልጣኞች የወሰኗቸው ውሳኔዎች ግን ቡድኑ ደካማ የውድድር ጊዜ እንዲያሳርፍ የራሱ ድርሻ ነበረው። ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ሶስት ነጥቦች ናቸው።

የቡድኑ አጨዋወት

 ቡድኑ በጥብቅ የሚከላከል ቢሆን አሁን እያስመዘገበው ካለው ውጤት የተሻለ ይሆን ነበር

ከባለፈው ዓመት የቡድን ስብስቡ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በመቀየር አዲስ ቡድን ገንብቶ ወደ ውድድር የቀረበው ደደቢት በአሰልጣኝ ኤልያስ መሐመድ እና ጌቱ ተሾመ ስር የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ ለመጫወት የሚሞክር ቡድን ነበር።

ምንም እንኳ በርግጠኝነት አሰልጥኞቹ የተከተሉት አጨዋወት ለውጤት መጥፋት ሁነኛ ምክንያት ነበር ብሎ መደምደም ባይቻልም ቡድኑ ዘግይቶ ወደ ቅድመ ውድድር እንደመግባቱ እና በመጀመርያው ዙር አጨዋወትም ብዙ የልምምድ ወቅት የሚያስፈልገው እና ረጅም የዝግጅት ወቅት የሚጠይቅ በመሆኑ ቡድኑ የአጨዋወት ጥብቅ መከላከል ያለ የተመሰረተ ቢሆን ቡድኑ ካስመዘገበው የተሻለ ነጥብ ሊያስመዘግብ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይህ ስንል ግን መከላከል አዋጪ እና ተመራጭ አጨዋወት ነው ማለታችን አይደለም።

ከላይ ከተጠቀሰው ምክንያት ውጭ ይህ ለማለት የሚያስደፍሩ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከነዛ ውስጥ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በጥራት ደረጃ ዝቅተኛ ጥራት ያላቸው የተጫዋቾች ስብስብ እና ትንሽ የቡድን ጥልቀት ያለው ቡድን ይዘው በጥብቅ መከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት መርጠው ዓመቱን ሙሉ ወገብ ላይ ሲቀመጡ እና ለዋንጫ ሲጫወቱ በተደጋጋሚ ጊዜ አይተናል። ለዚህ ሃሳብ እንደ ማሳያ የሚሆነን በ2009 በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ እየተመራ በውድድር ዓመቱ ጥሩ ውጤት ያመጣው ወልዲያ እና ባለፈው ዓመት በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመራ እስከ ውድድር ዓመት ፍጻሜ ለዋንጫ የተጫወተው መቐለ 70 እንደርታን ማየት ይቻላል። ቡድኖቹ በውድድር ዓመቱ ያሸነፏቸው ጨዋታዎች እና ያስቆጠሯቸው ግቦች ይዘውት ከጨረሱት ደረጃ ስናይ ቡድኖቹ የመረጡት አጨዋወት ከነበራቸው የቡድን ጥራት እና ጥልቀት ምንያህል አዋጪ እንደነበር እናያለን።

ከዚ ውጪ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚገኙት ክለቦች አብዛኞቹ በመከላከል ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ስላላቸው እንደ ደደቢት አይነት በደምብ ያልተደራጁ እና ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት የሚሞክሩ ቡድኖች ሲቸገሩ እና ውጤት አጥተው ሲወርዱ ይታያል። በ2008 በሊጉ ጥሩ ኳስ ሲጫወት የነበረው እና ከአሁኑ የደደቢት ስብስብ የተሻለ የተጫዋቾች ጥራት የነበረው አዲስ አበባ ከተማ ለዚህ ማሳያ ነው። ቡድኑ በሁለተኛው ዙር አጨዋወቱ ቀይሮ ያስመዘገበው ውጤትም ሌላ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

በነዚህ ምክንያቶችም ከላይ ከተጠቀሱት ቡድኖች ያነሰ የቡድን ጥራት እና ጥልቀት ያለው ደደቢት በዚህ ወቅት በሊጉ ላይ ለመቆየት በጠንካራ መከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ ቡድን ከመመስረት የተሻለ አማራጭ እንደሌለው መገመት ይችላል። በተጨማሪም ቡድኑ ባልተጠናው የኳስ አመሰራረት ሂደት ላይ በራሱ የግብ ክልል የሚያጠፋው ዘለግ ያለ ጊዜ እና ጥቅም አልባ ተደጋጋሚ የጎንዮሽ ቅብብል ምን ያህል ለተቃራኒ ቡድን ቀላል እንደሆነ ስታይ ቡድኑ ከአጨዋወቱ ጋር በደምብ እንዳልተላመደ መገንዘብ ይቻላል። በአጠቃላይ መስከረም 12 አከባቢ በአዲስ ስብስብ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸው የጀመሩት የደደቢት አስልጣኞች እጅግ በጥቂት ሳምንታት የዝግጅት ወቅት ውስጥ ያንን ጊዜ እና ጥራት የሚያስፈልገው አጨዋወት ለመተግበር መወሰናቸው ትልቅ ስህተት ነው ብዬ አስባለሁ። 

ደጋፊ አልባነት

፨ ቡድኑ ከከተማው የኳስ አፍቃሪ ጋር ለመቀራረብ የሰራው ስራ አነስተኛ በመሆኑ ቡድኑ እንደተፈለገው የሜዳ ድጋፍ እንዳያገኝ አድርጎታል

ይህ ሃሳብ እንዲሁ ሲታይ ውሃ የማያነሳ ሃሳብ ሊመስል ይችላል። ሆኖም በተፈጥሮ አንድ ደጋፊ አንድን ክለብ ለመደገፍ ከእግር ኳሳዊ ምክንያት ውጭ ከክለቡ ጋር መንፈሳዊ ትስስር (emottionl attachment) የሚፈጥርለት ነገር ይፈልጋል። ቡድኑ እንደ መቐለ 70 እንደርታ ያሉ በሊጉ በርካታ ደጋፊዎች ካሏቸው ክለቦች አንዱ የሚገኝበት ከተማ እንደመዘዋወሩ ቶሎ ደጋፊዎች ለማግኘት እንደሚከብደው ቢታወቅም ክለቡ ለአካባቢው ተስፈኛ ወጣቶች ዕድል ቢሰጥ አሁን ካለው በተሻለ ድጋፍ የሚያገኝበት ዕድል የሰፋ ነበር።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ደደቢት መቀመጫውን ወደ መቐለ የቀየረው በጥናት ላይ የተመሰረተ እና የደጋፊ ቁጥሩን ለመጨመር ያለመ ሳይሆን አስገዳጅ የፋይናንስ ሁኔታዎች ገፊ ምክንያት ሆነውበት ከውሳኔ መድረሱ በፍጥነት ደጋፊ ከማግኘት ጋር ወደተያያዙ ስራዎች እንዳያመራ ያደረገው ይመስላል። 

ከዛ ውጭ ታላላቆቹ የአውሮፓ ክለቦች በሩቅ ምስራቅ ያላቸው ተቀባይነትን ለመጨመር በቡድናቸው ይህን ያክል ልዩነት የማይፈጥሩ እንደነ ታኩማ አሳኖ፣ ርዮ ሚያይቺ፣ ፓርክ ቹ ያንግ፣ ሰን ጂ ሀይ እና ዶን ፋንግ ዙ የመሳሰሉ ተጫዋቾችን አስፈርመው ያገኙት ተቀባይነት እና የገበያ ጥቅም ሲታይ ደደቢት ከአካባቢው የሚገኙትን ወጣት ተጫዋቾች በቡድኑ ቢያካትት አሁን እያገኘው ካለው ድጋፍ የሚሻል ድጋፍ ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል።

ቅድመ ዝግጅት

 ቡድኑ በቅድመ ዝግጅት ላይ የሰጠው ትኩረት አናሳ ነበር 

ክለቡ በጣም ትልቅ እቅድ ይዞ እንደመነሳቱ ለእቅዱ መሳካት ያደረገው ቅድመ ዝግጅት አናሳ ነው። አመራሮቹ እንደዚህ የአንድን ክለብ ታሪክ መቀየር የሚችል ትልቅ ውሳኔ ትኩረት የሰጡበትም አይመስልም። ለዚህ ትልቅ ማሳያ ቡድኑ ለ2011 ውድድር ዓመት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ተጫዋቾች ያዘዋወረው በአንድ መስኮት ነው።

ቡድኑ ከባለፉት ዓመታት ጀምሮ ለዚህ “ትልቅ ፕሮጀክት ” ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ቢያደርግ እና ለዚህ አካሄድ የሚሆኑ ባለትንሽ ደሞዝ ተጫዋቾች በቡድኑ አካቶ የፕሪምየር ሊግ ልምድ እንዲይዙ ቢያደርግ ቡድኑ በልምድ እጦት ያጣውን በርካታ ነገር ማቃለል ይችል ነበር። በግማሽ ዓመት የዝውውር መስኮት ገሚሱን ስብስብ አሰናብተው በምትኩ አዳዲስ ተጫዋቾች ማምጣታቸውም የዓመቱ መጀመርያ ጥድፊያ በስህተት የተሞላ እንደነበር የሚያሳይ ነው። ይህ ነገር በዓመቱ መጨረሻ ድንገት የተፈጠረ ነገር ነው እንኳ ቢባል ቡድኑ አዲስ ቡድን ከመገንባቱ  እና ተጫዋቾች ከመመልመሉ በፊት በዝውውር ላይ ብዙ ስራ ማቃለል የሚችልለት የእግር ኳስ ዳይሬክተር አለመቅጠሩ ትልቅ ስህተት ነበር።

ቡድኑ በዓመቱ መጀመርያ በዝውውር ላይ የፈፀማቸው ትልቅ ስህተቶች በውጤት ላይ የራሱ አስተዋፅኦ ነበረው።

በአጠቃላይ ቡድኑ በዓመቱ መጀመርያ ላይ ለብዙ ቡድኖች ምሳሌ ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም በፋይናንሳዊ፣ በመሰረታዊ የአጨዋወት ምርጫ ስህተት እና ዝውውሮች በሰራቸው ትላልቅ ስህተቶች ከሊጉ መውረዱ አረጋግጧል።