የጅማ አባጅፋር ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን ይሆን?

በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ሊጉን በተቀላቀለበት ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን በ2010 ያነሳው ጅማ አባጅፋር በፋይናንስ ቀውስ የተነሳ እየታመሰ ይገኛል። ባሳለፍነው ሳምንት በሊጉ 26ኛ ሳምንት ጨዋታውን ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በሁለት አቻ ከተጠናቀቀ በኋላ ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ ልምምድ ያቋረጠ ሲሆን ረቡዕ በኢትዮጵያ ዋንጫ ከወላይታ ድቻ ጋር በሶዶ ከተማ ጋር ሊያደርግ የነበረውን ጨዋታ ፎርፌ መስጠቱ ይታወቃል።

አሁን እየተሰማ ያለው ደግሞ የፊታችን እሁድ ሶዶ ከተማ ላይ የሊጉ 27ኛ ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ለማከናወን ምንም አይነት እንቅስቃሴ በክለቡ በኩል አለመደረጉ በተመሳሳይ እንደ ኢትዮጵያ ዋንጫ ሁሉ በፕሪምየር ሊጉም ፎርፌ ሊሰጥ ነው ወይ? የሚባለው ጉዳይ በስፋት እየተነገረ ይገኛል።

እስካሁን ተጫዋቾቹ የሦስት ወር ደሞዝ አልተከፈለንም በማለት ልምምድ ሲያቋርጡ በክለቡ አመራሮች በኩል ችግሩ ምንድነው በማለት ተጫዋቾችን በመጥራት መፍትሄ ለመስጠት ጥረት አለመደረጉ አስገራሚ ነው። ቢያንስ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው ቢባል እንኳ የክለቡ አመራሮች ተጫዋቾቹ ወደ መደበኛ ልምምዳቸው እንዲመለሱ ጥረት አለማድረጋቸው የክለቡ አመራሮች ቸልተኝነትን ያሳያል።

የአንድ ወር ደሞዝ በመክፈል ተጫዋቾቹን ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ምናልባትም ዛሬ ይሄን ክፍያ ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ሰምተናል። አሁን ክለቡ ይህን ችግር ተሸፋፍኖ ለማለፍ የሚያደርገው ጥረት ሊሳካለት ቢችልም እየተንከባለለ የክለቡን አካባቢ ሲያውክ የቆየው የፈይናንስ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምን ታስቧል? ቀጣይ እጣ ፈንታውስ ምንድነው? የሚለው ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡